በኡጋንዳ የስደተኞች ቁጥር መጨመሩ ጫና እያሳዳረ ነው ተባለ

በኡጋንዳ የስደተኞች ቁጥር በፍጥነት መጨመሩ በሀገሪቱ ላይ ጫና እያሳዳረ ነው ተባለ፡፡

በዚህ ዓመት ብቻም ከ25 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች ከዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ወደ ኡጋንዳ ገብተዋል፡፡

በአጠቃላይ ሀገሪቱ ከ345 ሺህ በላይ የኮንጐ ስደተኞች ያቀፈች ሲሆን፣ ይህም ቁጥር እሳካሁን ከታየው የስደተኞች ቁጥር ሁለተኛው ትልቁ ቁጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስደተኞቹን ሳንቀበል የዋልንበት ቀን የለም ፤ ባለፈው ሳምንት ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብቻ ከ1ሺህ በላይ ስደተኞችን ተቀብለናል ሲሉ የተናገሩት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ የሆኑት ዳኒያ አስላም ካሀን ናቸው ፡፡

የኡጋንዳ የስደተኞች ቁጥር እ.ኤ.አ. ከ 2016 ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር አሁን ላይ ከአንድ ሚልየን በላይ ደርሷል ፡፡

ከ825 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች በዚያው በኡጋንዳ እንደሚገኙና ከብራዚል፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ 105 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች በስደት ይኖሩባታል፡፡

ይህ የስደተኞች እንቅስቃሴ ለኢቦላ ወረርሽኝ ስጋትም ዳርጓታል ነው የተባለው፡፡

ወደ ሀገሪቱ ከሚገቡት ስደተኞች አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ስደተኞች በከፍተኛ ሁኔታ በኢቦላ ወረርሽኝ ከተጠቁ አከባቢዎች ናቸው ፡፡

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እ.ኤ.አ. ከነሐሴ ወር 2018 ጀምሮ በኢቦላ ወረርሽኝ ምክንያት 332 ሰዎች በኢቦላ  ወረርሽኝ መጠቃታቸው  እና በግንቦት ወር አጋማሽ እስከ ሰኔ 2019 ባለው ጊዜ ወስጥ ደግሞ 20 የሚሆኑ አዳዲስ የበሽታው ክስተቶች በሀገሪቱ ታይተዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር  ካሀን  እንደተናገሩት በሁሉም የስደተኞች መቀበያ ማዕከላት ውስጥ  የኢቦላ ወረርሽኝ ቅድመ ምርመራ ማካሄዳቸውን ተናግረው ከኡጋንዳ መንግስት ጋር በርካታ የመቆጣጠሪያ ተቋማትን ለማቋቋም እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የአገሪቱ ከአቅም በላይ እየሆነ የመጣው የስደተኞች ቁጥር ለስደተኞቹ የሚደረገውን  ምላሽ የተገደበ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡

"የገንዘብ ድጋፍ ትልቅ ጉዳይ ነው ያሉት ኮሚሽነር  ካሀን፣ ይሁን እንጂ ያለን በጀት  አፋጣኝ የሰብአዊ ምላሾችን ከመስጠት አኳያ እቅዶቻችንን ለማሳካት በቂ አይደለም” ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ በ2019 በኡጋንዳ ላሉ ስደተኞች ምላሽ ለመስጠት   927 ሚሊየን ዶላር ያሥፈልጋል ብሏል፡፡

ከዚህ በጀት ውስጥ ውስጥ እስካሁን 150 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው የተገኘው፡፡

(ምንጭ፡-አልጀዚራ)