በቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ያያ ጃሜ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

የጋምቢያ መንግሥት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ያያ ጃሜ የተፈፀሙ የጾታ ጥቃቶችን ዜጎች ሪፖርት በማድረግ እንዲተባበሩ ጥሪ አቀረበ። 

ጥሪው ለሁሉም ልጃገረዶችና ሴቶች የቀረበ ሲሆን ይህ ውሳኔ የተላለፈው የቀድሞዋ የቁንጅና ንግስት ቱፋ ጃሎው ለቢቢሲ በ2015 በፕሬዝዳንቱ መደፈሯን ከተናገረች በኋላ ነው።

ቢቢሲ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ፕሬዝዳንቱ በአሁኑ ሰዓት በኢኳቶሪያል ጊኒ በስደት የሚኖሩ ሲሆን፣ የፓርቲያቸው ኤፒአርሲ ቃል አቀባይ ግን የቀረበውን ክስ ክዷል።

ቃል አቀባዩ ኡስማን ራምቦ ጃታ ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ "እንደ ፓርቲ እና እንደ ጋምቢያ ህዝብ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ በሚቀርቡ መሠረተ ቢስ ውንጀላዎች ተሰላችተናል" ብለዋል።

"የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለእንዲህ አይነቱ ውሸትና የጥላቻ ዘመቻ መልስ ለመስጠት ጊዜ የላቸውም" ሲሉ የተናገሩት ደግሞ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ናቸው።

የጋምቢያ ጠቅላይ አቃቢ ህግ የሆኑት አቡበከር ታምባዱ በመግለጫቸው ላይ የቱፋ ጃሎውን ጥንካሬ አድንቀዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ያያ ጃሜ የተጣለባቸውን ኃላፊነት አላግባብ ተጠቅመዋል በማለት በእርሳቸው ላይ ጾታዊ ትንኮሳ እና የመድፈር ጋር ተያይዞ ይፋ የሆነውን ሪፖርት በመጥቀስ "የተዋረደ ተግባር" ሲሉ የፕሬዝዳንቱን ተግባር ኮንነውታል።

ያያ ጃሜ በ22 ዓመት የስልጣን ቆይታቸው ስለፈፀሟቸው ጾታዊ ትንኮሳዎችና ደፈራዎች የሚያጠና ኮሚሽንም ተቋቁሟል።

የአሁኑ ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው ያያ ጃሜ ተላልፈው እንዲሰጧቸው ለመጠየቅ የዚህን ኮሚሽን ሪፖርት ውጤት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ፋቱ ጃሎው ፕሬዝዳንቱን ያገኘቻቸው በስማቸው በተዘጋጀው የቁንጅና ውድድርን በበላይነት አሸንፋ ሲሆን እድሜዋም 18 ነበር።

ይህንን ውድድር ባሸነፈችበት ወር ፕሬዝዳንቱ የተለያዩ ስጦታዎችን እና ገንዘብ የሰጧት ሲሆን አክለውም ቤተሰቦቿ በሚኖሩበት አካባቢ ውሃ እንዲገባ በማስተባበር ቅርበታቸውን አጠናከረዋል።

ከዛም ትላለች ፋቱ ለፕሬዝዳንቱ ድጋፍ ለማሰባሰብ በተዘጋጀ በአንድ የእራት ግብዣ ላይ የጋብቻ ጥያቄ አቀረቡላት። ፋቱ ግን ጥያቄውን በመቃወም በእራት ግብዣው ላይ ለመስራት የወሰደቻቸውን ኃላፊነቶችን ሰረዘች።

በ2015 ሰኔ ወር ላይ ግን በፕሬዝዳንቱ ቤተመንግሥት በተካሄደ ሀይማኖታዊ ፕሮግራም ላይ እንድትገኝ ተጠየቀች። ቤተመንግሥቱ እንደደረሰች ግን የተወሰደችው ወደ ፕሬዝዳንቱ የግል መኖሪያ ነው።

"ምን እንደሚፈጠር ግልፅ ነበር" ትላለች ፋቱ፤ ፕሬዝዳንቱ የጠየቁትን እምቢ በማለቷ መናደዳቸውን በማስታወስ። ከዛም በጥፊ እንደመቷትና እንደደፈሯት፤ መርፌም እንደወጓት ታስታውሳለች።

ቱፋ ጃሎው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ያያ ጃሜ ፍርድ ቤት ቀርበው ለፈፀሙት ጥፋት እንዲቀጡ ትፈልጋለች። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)