በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የዓለም የጤና ስጋት ነው ተባለ

የዓለም ጤና ድርጅት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ "በአስቸኳይ የዓለምን ትኩረት የሚሻ የጤና ቀውስ" ሲል በይኖታል።

ይህ የጤና ድርጅቱ ውሳኔ ሐብታም አገራት ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚረዳ ገንዘብ እንዲሰጡ ያስችላቸው ይሆናል ተብሏል።

ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት አሁንም አገራት ድንበራቸውን እንዲዘጉ ያለው ምንም ነገር የለም። ለዚህ ምክንያት ብሎ ያቀረበው በሽታው ከክልሉ ወጥቶ የመዛመት እድሉ አናሳ ነው በሚል ነው።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እስካሁን ድረስ በወረርሽኙ ምክንያት 1 ሺህ 600 ሰዎች ሞተዋል።

በዚህ ሳምንት ሚሊየኖች በሚኖሩባት ጎማ በበሽታው የተያዘ ቄስ መሞቱ ተሰምቷል።

ጎማ በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ድንበር የምትገኝ ከተማ ስትሆን፣ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ያለባት ስፍራ ነች።

ወረርሽኙ በዚች ከተማ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት "ሁኔታውን ሊቀይር የሚችል" ያለው ሲሆን፤ ከጎማ ውጪ ግን ስለመዛመቱ እስካሁን የተሰማ ነገር የለም።

ይህ የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠው የአስቸኳይ ምላሽ ጥሪ ከፍተኛው ሲሆን፣ ድርጅቱ ከዚህ በፊት ሦስቴ ብቻ እንዲህ አይነት ጥሪዎችን አስተላልፏል።

ከእነዚህም መካከል አንዱ ከ2014 እስከ 2016 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በምዕራብ አፍሪካ የኢቦላ ወረርሽኝ ተከስቶ 11 ሺህ ሰዎችን በገደለበት ወቅት ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በጄኔቫ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅትና አስቸኳይ ትኩረት እንደሚሻ ባወጁበት መግለጫ ላይ "ጊዜው ዓለማችን ማስጠንቀቂያውን የሚወስድበት ነው" ብለዋል።

የጉዞ ገደብ ሊደረግ እንደማይገባ የተሰጡ ምክረ ሀሳቦችን ድርጅቱ መቀበሉን የተናገሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ አክለውም ንግድ፣ እንዲሁም ወረርሽኙ በተከሰተበት አካባቢ ከሚገኙ አገራት ውጪ በአየር መንገድና ወደብ መግቢያዎች ላይ የሚደረግ የጤና ፍተሻም መኖር የለበትም ሲሉ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ድርጅቶች ይህንን ውሳኔ በመልካም ጎኑ የተቀበሉት ሲሆን፣ " በወረርሽኙ የተጠቁ ግለሰቦችንና ቤተሰቦቻቸው ሕይወት ላይ ለውጥ ባያመጣም ዓለም ለዚህ የጤና ቀውስ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይኖርበታል" ብለዋል በመግለጫቸው።

የኢቦላ ወረርሽኙ በዓለማችን ታሪክ ከተከሰቱት ሁለተኛው ሲሆን በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሁለት አውራጃዎች በስፋት ተከስቷል።

እስካሁን ከ2500 ሰዎች በላይ የተያዙ ሲሆን፣ ከዚህም አብዛኞቹ ሞተዋል። በየእለቱ 12 አዳዲስ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ይገኛሉ።

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1ሺህ ለመድረስ 224 ቀናት ብቻ የፈጀበት ሲሆን 2ሺህ ለመድረስ ግን ተጨማሪ 71 ቀናት ብቻ ናቸው የወሰደበት።

ከዚህ ቀደም ከተከሰተው ወረርሽን ወዲህ እጅግ ውጤታማ የሆነ ክትባት የተገኘ ሲሆን፣ በበሽታው የተያዙ አልያም ከተያዘ ሰው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸው 161 ሺህ ሰዎችም ክትባቱ ተሰጥቷቸው ከበሽታቸው ተፈውሰው ነበር።

ነገር ግን ሁሉም ሰው ስላልተከተበ ወረርሽኙ በድጋሚ ሊከሰት ችሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙ በተከሰተበት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዙሪያ ወደሚገኙ ሀገራት የመዛመት እድሉ ከፍተኛ ነው ያለ ሲሆን፣ እስካሁን ኡጋንዳና ሩዋንዳ ውስጥ በሽታው መከሰቱ ታይቷል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)