ረሃብን ከአፍሪካ ለማስወገድ የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል- ፕሬዚዳንትፖል ካጋሚ

ረሃብን ከአፍሪካ ለማስወገድ የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሚ ገለፁ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት በሩዋንዳ እስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለውና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ላይ ባተኮረው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነው፡፡

በአውሮፓውያኑ 2025 አፍሪካ ረሃብን ለማስወገድ በማላቡ ስምምነት ላይ የገባችውን ቃል እየጠበቀች አትገኝም፣ይህን በማሳካት በኩልም ከመስመር ወጥታለች ብለዋል ፖል ካጋሚ፡፡

ይህ ችግር በትብብር ፣ በተቀናጀ ጥረት እና ተገቢውን ቴክኖሎጂ ሁሉ በመጠቀም ብቻ ሊቀረፍ እንደሚችልም ነው አፅንዎት የሰጡት፡፡

የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ፈተና እዚህ ሩዋንዳም ተደቅኖብናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይሁንና ተገቢውን እውቀት በተገቢው የሰው ሃይልና ቴክኖሎጂ በማቀናጀት እንሰራለን፣ በትብብር ከተንቀሳቀስን ደግሞ ችግሩ የማይቀረፍ አይደለም ብለዋል፡፡

ይህን አለምአቀፍ የምክክር መድረክ የሩዋንዳ መንግስት ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣አለም ባንክ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና እርሻ ድርጅትና ሌሎችም በትብብር እንዳሰናዱት ሲጂቲኤን በዘገባው አመልክቷል፡፡