በኬንያ ሠርግ ከታደሙ መካከል አንድ ሰው በኮሌራ ሲሞት 40 ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸው ተገለጸ

በኬንያ መዲና ናይሮቢ ባለፈው ቅዳሜ በተከናወነ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ከታደሙት መካከል አንድ ተጋባዥ በኮሌራ ሳቢያ ሕይወቱ ሲያልፍ ሌሎች 40 የሚሆኑት ለሕክምና ሆስፒታል መግባታቸውን ዘ ስታር የተባለው ጋዜጣ ዘገበ።

ጋዜጣው ጭምሮ እንደገለፀው የሠርጉ ተጋባዦች የሕክምና ምርመራ ውጤት እንደሚያሳየው ተጋባዥ እንግዶቹ ሠርጉን ከታደሙ በኋላ ለኮሌራና የምግብ መመረዝ እንደተዳረጉ ያሳያል።

አዲስ ተጋቢ ጥንዶቹ ግን ምንም ዓይነት የጤና መቃወስ ያልገጠማቸው ሲሆን፣ በሠርጋቸው ዕለትም ለጫጉላ ሽርሽር ወደ ዱባይ በረዋል።

ይሁን እንጂ የሙሽራው አያት በዚሁ ምክንያት ባሳለፍነው ማክሰኞ ሕይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።

በሠርግ ሥነ ሥርዓቱ ላይ 450 የሚሆኑ እንግዶች ተጋብዘው እንደነበር ጋዜጣው አስፍሯል።

የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ አሠናጅ ይህ ችግር እንዴት ሊከሰት እንደቻለ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ኮሌራ በዲያሪያ ኢንፌክሽን የሚመጣ ሲሆን ባክቴሪየም ቫይብሪኦ ኮሌራ በተባለ በሽታ አምጭ ተህዋስ ምግብና ውሃ ሲመረዝ ይከሰታል።

በኬንያ የኮሌራ በሽታ መከሰት የተለመደ ባይሆንም ከሁለት ዓመታት በፊት ግን በመዲናዋ በአንድ ሆቴል በተካሄደ ዓለም አቀፍ የጤና ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ላይ ወረርሽኙ ተከስቶ እንደነበር ተነግሯል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።