የኬንያው ፕሬዚደንት ጳጉሜ 2 እና 3 በአዲስ አበባ በሚካሄደው የሰላም ፌስቲቫል ላይ እንደሚሳተፉ አስታወቁ

የኬንያው ፕሬዚደንት ጳጉሜ 2 እና 3 በአዲስ አበባ በሚካሄደው የሰላም ፌስቲቫል ላይ እንደሚሳተፉ አስታወቁ

ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ከሀገር አቀፍ የአንድነት፣ ይቅርታና ሰላም ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እና የኮሚቴው አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ኢትዮጵያውያን በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆነው የማይለወጡ እና ለድርድር የማይቀርቡ የኬንያውያን ወዳጆች ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከቅድመ-ነጻነት ጊዜ ጀምሮ የኬንያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ እንደሆነች አስታውሰው፤ በጳጉሜን 2 እና 3፣ 2011 ዓ.ም. በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የአንድነት፣ ይቅርታና ሰላም ፌስቲቫል ላይ እንደ ኢትዮጵያውያን ሆኜ እገኛለሁ ብለዋል።

መሪዎች ለሕዝቦቻቸው ሰላም እና ብልፅግናን እንጂ ውድቀትና ጥፋትን ማውረስ አይገባም ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

የሀገር አቀፍ የአንድነት፣ ይቅርታና ሰላም ፌስቲቫሉን ያዘጋጀው እና በበጎ ፈቃድ የተቋቋመው የሀገር አቀፍ የአንድነት፣ ይቅርታና ሰላም ኮሚቴ አባላት ፕሬዚደንትዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፤ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ በኢትዮጵያ በሚካሄደው የሰላም ፌስቲባል ላይ እንዲታደሙ ጋብዘዋቸዋል።

ኬንያ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገር መሆኗን ያወሱት ዶ/ር ሙላቱ፤ ከኬንያ ግጭትን የማስወገድ ተሞክሮ እንዲያጋሩም ጠይቀዋል።

ከፕሬዚደንቱ በተጨማሪ ለቀድሞ የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራኢላ ኦዲንጋ በፌስቲቫሉ ላይ እንዲሳተፉ ግብዣ የቀረበላቸው ሲሆን፤ ለመሳተፍ ቃል ገብተዋል።

ሀገር አቀፍ የአንድነት፣ ይቅርታና ሰላም ኮሚቴ ሰላሟ እና ልማቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚል ዓላማ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከኃይማኖት ተቋማት፣ ከስነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ከወጣቶች እና ከሲቪል ማህበረሰብ አባላት የተዋቀረ ኮሚቴ ነው።