ታንዛኒያ ከ200 ሺህ በላይ የብሩንዲ ስደተኞችን ልታስወጣ ነው

በታንዛንያ የሚገኙ ከ200 ሺህ በላይ የብሩንዲ ስደተኞች እስከመጭው ጥቅምት ወር ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ካልሆነ ግን በግድ እንደሚመለሱ የታንዛኒያ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጹ።

ሚንስትሩ ካንጊ ሉጎላ "አሁን በብሩንዲ ሰላም አለ፤ በመሆኑም እስከ መጭው ጥቅምት ወር ድረስ ስደተኞቹ ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው፤ ከዚያ በኋላ ግን ፈለጉም አልፈለጉም እንመልሳቸዋለን " ብለዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት በብሩንዲው ፕሬዚደንት ፒዌሬ ንክሩንዚዛ ለሦስተኛ ጊዜ በምርጫ ማሸነፋቸውና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራን ተከትሎ በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በርካታ ብሩንዲያዊያን ወደ ጎረቤት ሃገራት ተሰደዋል።

ስደተኞቹ በታንዛኒያ ደቡብ ምዕራብ ግዛት ኪጎማ፤ ኒያሩጉሱ፣ ንዱታ እና ምቴንደሊ የስደተኛ ማቆያ መጠለያ ተጠልለው ይገኛሉ።

ታንዛኒያ ስደተኞችን ወደ መጡበት አገር አስገድዶ መላክን በሚከለክለው የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት አባል ናት።

ይሁን እንጂ የውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ሉጎላ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ባለፈው ዓመት በየቀኑ 2 ሺህ ስደተኞች ለመመለስ በታንዛኒያና በብሩንዲ መካከል የተደረገውን ስምምነት አላከበረም ሲል ወቅሰዋል።

ባሳለፍነው አርብ ሉጎላ ከብሩንዲ አቻቸው ፓስካል ባራንዳጊየ፤ በነዱታ የሚገኘውን የስደተኞች መጠለያን የጎበኙ ሲሆን ስደተኞቹ ወደ ሃገራቸው የማይመለሱ ከሆነ ከበድ ያለ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስጠንቅቀዋል።

አንድ ስሙ እንዳይገለፅ የጠየቀ ስደተኛ ለቢቢሲ እንደተናገረው ወደ ብሩንዲ ለመመለስ ደህንነት እንደማይሰማው ተናግሯል።

"ውሳኔው ያልተጠበቀ ነው፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወይም ታንዛኒያ የኒክሩንዚዛ መንግሥት በዜጎቹ ላይ እስር እንዳይፈፅም ምን ሰራ ? ግድያ አለ፤ ጠለፋ አለ፤ አስክሬን ይገኛል፤ የሚመልሱን እንድንገደል ነው" ሲል ስጋቱን ገልጿል።

የዓለም አቀፉ ስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) ቃል አቀባይ ዳና ሁግሄስ፤ ሁለቱ ሃገራት ዓለም አቀፉን ስምምነት እንዲያከብሩና የስደተኞችን መብት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

ቃል አቀባይዋ እንዳሉት ድርጅቱ በታንዛኒያ የብሩንዲ ስደተኞች በፈቃደኝነት ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ በሚደረገው ሂደት ተሳትፈው እንደነበር አስታውሰው በእያንዳንዱ ቀን 100 አዲስ ስደተኞች ከብሩንዲ ወደ ታንዛኒያ እንደሚገቡም አክለዋል።