በኬንያ ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ጉብኝት ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች በጎርፍ ተወሰዱ

በአንድ የኬንያ ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ጉብኝት ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች በደራሽ ጎርፍ በመወሰዳቸው የሁለቱ ህይወታቸው ማለፉ ሲረጋገጥ አምስቱ ደግሞ የገቡበት አልታወቀም ተብሏል።

የኬንያ ዱር እንስሳት መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው፣ አደጋው ያጋጠመው 'ሂልስ ጌት' ተብሎ በሚታወቀው ብሄራዊ ፓርክ ሲሆን፣ አምስት ኬንያውያን ጎብኚዎች፣ አንድ የውጭ ዜጋና አንድ አስጎብኚ ናቸው በደራሽ ጎርፍ የተወሰዱት።

ከጎርፉ በኋላ በተደረገ አሰሳ የሁለቱ ሰዎች አስክሬን የተገኘ ሲሆን፤ ቀሪዎቹን ሰዎች የማፈላለጉ ስራ ደግሞ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።

በአደጋው ምክንያትም ፓርኩ ለጊዜው ዝግ እንዲሆን ተደርጓል ነው የተባለው።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው አደጋው ያጋጠማቸው ጎብኚዎች ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ በ100 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኘውን ብሄራዊ ፓርክ ለመጎብኘት በ12 ምድቦች ተከፍሎ ብሄራዊ ፓርኩን ሲጎበኝ የነበረ ቡድን አባላት ናቸው።

አንድ የኬንያ ዜና አውታር እንደዘገበው ደግሞ ከጎብኚዎቹ መካከል በህይወት መትረፍ የቻለ አንድ ግለሰብ ወደ ፓርኩ ሃላፊዎች ጉዳዩን በማሳወቁ ወዲያው የፍለጋ ስራው መጀመሩ ተገልጿል። ፍለጋውን እንዲያግዝም አንድ ሄሊኮፍተር ተመድቧል ነው የተባለው።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ የፖሊስ አባል እንደገለጸው በቦታው የነበሩ ሰዎችን አስተያየት ከግምት ውስጥ በማስገባት እስካሁን ያልተገኙት ሰዎች በህይወት ይኖራሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም ብሏል።

'ሂልስ ጌት' የተባለው ፓርክ ከብዙ ሺ ዓመታት በፊት የነበሩ ሃይቆችን የሚመመግቡ ወንዞችና ጎርፎች የሚያልፉበት አካባቢ ስለሆነ ለእንደዚህ አይነት አደጋዎች በእጅጉ የተጋለጠ ነው። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)