የናይጀሪያ ፖሊስ በሌጎስ ‘የሕፃናት ማምረቻ’ ናቸው ያላቸውን ቤቶች በቁጥጥር ሥር አዋለ

የናይጀሪያ ፖሊስ ሌጎስ ውስጥ ‘የሕፃናት ማምረቻ’ በሚል በገለፃቸው ቤቶች ላይ በከፈተው ዘመቻ 19 ነፍሰ ጡር ሴቶችን ነፃ ማውጣቱ ታውቋል።

አብዛኞቹ ሴቶች “አርግዘው እንዲወልዱ ለማድረግ እና ልጆቻቸውን ለመሸጥ ዓላማ” በጠለፋ የተያዙ መሆናቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በቦታው ላይ እንደ ነርስ የሚያገለግሉ ሁለት ሴቶች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ቢሆንም ዋነኛው ተጠርጣሪ እንዳልተያዘ ታውቋል።

በፖሊስ መረጃ መሠረት ወንድ ሕፃናት 1400 ዶላር ሲሸጡ፣ ሴት ሕፃናት ደግሞ በ830 ዶላር ለገበያ ይቀርባሉ።

ሕፃናቱ ወደ ሌላ ሥፍራ የሚጓጓዙ መሆኑ ቢታወቅም ዋነኞቹ ገዥዎች እነማን እንደሆኑ ግን አልታወቀም ብሏል መረጃው።

‘የሕፃናት ማምረቻ’ የሚለው ጉዳይ ናይጀሪያ ውስጥ የተለመደ ሲሆን፣ ይህን ድርጊት ለማስቆም ከተካሄዱ በርካታ ዘመቻዎች መካከል ባለፈው ዓመት 160 ሕፃናት ነፃ የወጡበት ይገኝበታል።

በአሁኑ ዘመቻ አራት ሕፃናት ነፃ መውጣታቸው ተገልጿል።

በአገሪቱ ዋና ከተማ ሌጎስ ውስጥ የተገኙት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 28 የሆኑት ልጃገረዶች እና ሴቶች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሥራ ትቀጠራላችሁ ተብለው የመጡ እና በአንድ ግቢ ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርገው የተደፈሩ መሆናቸው ታውቋል።

በአሁኑ ወቅት ነፃ የወጡት ሴቶች እና ሕፃናት ወደ ሌላ ሥፍራ ተዛውረው እያገገሙ መሆኑን ፖሊስ ተናግሯል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)