ኡጋንዳ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ላይ የሞት ቅጣት ልትጥል ነው

የኡጋንዳ ስነ-ምግባርና ግብረገብነት ሚኒስትር እ.አ.አ. በ2014 ቀርቶ የነበረውን የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎችን በሞት የሚቀጣውን ህግ በድጋሚ ሊያስተዋውቅ መሆኑን ገለጸ።

ሚኒስትሩ ሲሞን ሎኮዶ አዲሱ ረቂቅ ወደ ህግነት ሲቀየር የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ሲፈፅሙ የተገኙ የሞት ፍርድ ይጠብቃቸዋል ብለዋል።
''አሁን በስራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ህጋችን ውስንነት ይታይበታል። ተግባሩ ወንጀል መሆኑን ብቻ ነው የሚገልጸው። በዚህ ተግባር ተሰማርቶ የሚገኝ ማንኛውም ሰው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ማድረግ እንፈልጋለን። ጥፋተኛ የተባሉትም የሞት ፍርድ ይፈረድባቸዋል።''
ሚኒስትሩ አክለውም ''የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ለኡጋንውዳውያን ተፈጥሯዊ አይደለም። የዚሁ ሃሳብ አቀንቃኞች በትምህርት ቤቶች ጭምር ተፈጥሯዊና ምንም ችግር የሌለው ነው በማለት አባላትን ሲመለምሉ ነበር'' ብለዋል።
በ2014 የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ረቂቅ ህጉን ለማጽደቅና ጠበቅ ያለ ቅጣት እንዲኖር ፊርማቸውን ቢያኖሩም በዛው ዓመት የሃገሪቱ ሕገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ውድቅ አድርጎት ነበር።
ሲሞን ሎኮዶ እንደገለጹት ረቂቅ ህጉ በመጪዎቹ ሳምንታት ለተወካዮች ምክር የሚቀርብ ሲሆን፣ በአሁኑ ግን የፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ እና የህዝብ ተወካዮችን ድጋፍ አግኝቷል።
ለህዝብ ተወካዮች ቀርቦም ሁለት ሶስተኛ ድምጽ አግኝቶ ተግባራዊ እንደሚሆን እንገምታለን ሲሉ ተደምጠዋል ሚኒስትሩ።
ከአምስት ዓመት በፊት ሃገሪቱ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ስትጀምር አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት የቪዛ ክልከላ፣ ድጋፍ ማቆምና ወታደራዊ ልምምድ እስከ ማገድ ደርሰው ነበር።
ሚኒስትሩ ግን ማንኛውም አይነት ምላሽ እንደማያስቆማቸውም ሲገልፁ ''ማንም እንዲያስፈራራን አንፈቅድም። እርምጃው በተለይ በበጀትና አስተዳደር ዙሪያ ያሉ ደጋፊዎቻችንን እንደሚያስቆጣ እናውቃለን። ነገር ግን የእኛ ያልሆነ ባህልን ሊጭኑብን ለሚያስቡ ሰዎች አንገታችንን ደፍተን ማሳየት አንፈልግም'' ብለዋል ሲል ሮይተርስን ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ ዘግቧል።