በፅንስ ማቋረጥ ታስራ የነበረችው ሞሮካዊቷ ጋዜጠኛ ምህረት ተደረገላት

ሞሮካዊቷ ጋዜጠኛ ከጋብቻ በፊት ወሲብ በመፈፀም እንዲሁም በፅንስ ማቋረጥ አንድ አመት ተፈርዶባት የነበረ ቢሆንም የሞሮኮው ንጉስ መሃመድ አራተኛ ምህረት እንዳደረጉላት የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

የሃገሪቱ ፍትህ ሚኒስትር በእንደዚህ አይነት ጉዳይ የንጉሱ ጣልቃ መግባት "ርህራሄቸውና ምህረታቸውን የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

የ28 አመቷ ጋዜጠኛ ሃጃር ራይሱኒ በትናንትናው ዕለት ከእጮኛዋ ጋር ከእስር ቤት ስትወጣ ጣቶቿን ከፍ አድርጋ የድል ምልክት አሳይታለች።
እጮኛዋም ምህረት ተደርጎለታል ተብሏል። በሞሮኮ ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ወሲብ እንዲሁም ፅንስ ማቋረጥ ወንጀል ነው።

ምንም እንኳን መንግሥት ለእስሯ የሰጠው ምክንያት የፅንስ ማቋረጥና ከጋብቻ በፊት የሚፈፀም ወሲብ ቢሆንም፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በበኩላቸው በነፃ ጋዜጣ ላይ የተደረገ አፈና ነው ብለዋል።
ጋዜጠኛዋ መንግሥትን በመተቸት በሚታወቀው አክባር አል ያውም ነው የምትሰራው።

በነሐሴ ወር ከሱዳናዊ እጮኛዋ ጋር ከማህፀን ክሊኒክ ስትወጣ የታየች ሲሆን፤ የፅንስ ማቋረጡን ክስም አልተቀበለችም።

ወደ ክሊኒኩ የሄደችውም ያጋጠማትን መድማት ለመታከም እንደሆነ ተናግራ ነበር።

ክሱንም ሆነ ውሳኔውን ፖለቲካዊ ፍርድ ነው ብላ ያወገዘች ሲሆን መስከረም ወር ላይ አንድ አመት እንድትታሰር ተወስኖባት ነበር።

ጉዳዩን የያዘው አቃቤ ህግ በበበኩሉ የጋዜጠኛዋ እስር ከስራዋ ጋር እንደማይገናኝና የሄደችበት ክሊኒክም በህገወጥ ፅንስ ማቋረጥ ጥርጣሬ በፖሊስ ክትትል ሲደረግበት የነበረ ነው ብሏል።

እጮኛዋም አንድ አመት ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን በዶክተሩ ላይ ሁለት አመት እስር ተወስኖበታል። የዶክተሩ ረዳትም ሆነ ነርስ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙም የሙያ ፈቃዳቸውን ለተወሰነ ጊዜ በማገድ ብቻ ታልፈዋል።