አሜሪካ በአይነቱ ጠንካራ የተባለለትን ማዕቀብ በኢራን ላይ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቷን አስታውቃለች

አሜሪካ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአይነቱ ጠንካራ የተባለለትን ማዕቀብ በኢራን ላይ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቷን አስታውቃለች፡፡

በኢራን የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአይነቱ ጠንካራ የተባለለትን ማዕቀብ በነዳጅ ሃብቷ በበለጸገችው ሀገር ላይ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቷን ነው አሜሪካ ያስታወቀችው፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን ''ሞት ለ አሜሪካ'' የሚሉ መፈክሮችን ይዘው  ተቃውሞአቸውን በአደባባይ አሰምተዋል፡፡

የኢራን የወታደራዊ ኃይልም የሃገሪቱን የመከላከያ ብቃት ለማስመስከር አየር ኃይሉ ልምምዶችን እንደሚያደርግ ጠቁሟል።

እ.አ.አ በ2015 አሜሪካ እና ኢራን ያደረጉትን የኒውክሌር ስምምነት ተከትሎ ከኢራን ላይ ተነስተው የነበሩ ማዕቀቦች በድጋሚ ተግባራዊ እንዲደረግ የትራምፕ አስተዳደር እየሰራ ስለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን ማዕቀቡ ኢራንን ጨምሮ ከሀገሪቱ ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው ሀገራትን ኢላማ ያደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ይተላለፋል ተብሎ የሚጠበቀው ማዕቀብ የባንክ፣ የነዳጅ እና የመርከብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ ያነጣጠረ ስለመሆኑም ዘገባው አመላክቷል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ የሚጣለው ማዕቀብ በአይነቱ ለየት ያለና ጠንካራ ማዕቀብ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ አላማውም ኢራንን የኒውክሌር ፍላጎት መቀልበስ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የትራምፕ አስተዳደር ኢራን የሳይበር ጥቃቶችን፣ የሚሳዔል ሙከራዎችን እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ሚሊሻዎችን እና የሽብር ቡድኖችን መደገፍ ማቆም አለባት ሲልም ይሞግታል።

ይህ በኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር የዘርፉ ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ ማዕቀቡ ከ700 በላይ ግለሰቦችን፣ ድርጅቶችን፣ መርከቦችን እና አውሮፕላኖችን በዝርዝር እንደሚያካትት ገልጸዋል፡፡

ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ማዕቀቡን ተከትሎ ራሳቸውን ከኢራን ማግለላቸውን የጠቆሙት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱ ዋነኛው የገንዘብ ምንጭ የሚገኝበት የነዳጅ ምርትም በቀን በአንድ ሚሊዮን በርሜል መቀነሱን አስታውቀዋል።

አለም አቀፍ ክፍያዎችን የሚያከናውነውና መቀመጫውን በቤልጄም ብራሰልስ ያደረገው ስዊፍት ኔትዎርክ የተባለው የገንዘብ ተቋምም ማዕቀቡ ካነጣጠረባቸው የኢራን ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነትን እንደሚያቋርጥ ይጠበቃል፡፡ ይህ ውሳኔም ኢራንን ከአለም አቀፉ የፋይናንስ ስርአት እንደሚያገላት እየተነገረ ይገኛል፡፡

የኢራኑን የኒውክሌር ስምምነት ጠብቀው እየሄዱ ካሉ አምስት ሀገራት ውስጥ እንግሊዝ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ ማዕቀቡን የተቃወሙ ሲሆን ከኢራን ጋር ህጋዊ የንግድ ልውውጥ ማከናወን የሚሹ የአውሮፓ ኩባንያዎች ማዕቀቡ ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው የተለያዩ የክፍያ ስርዓቶችን እንደሚዘረጉ ቃል ገብተዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በስም ያልጠቀሷቸው ስምንት የአሜሪካ ወዳጅ ሃገራት ከኢራን ነዳጅ እንዲያስገቡ ፈቅደዋል።

ከነዚህ ሀገራት መካከልም ጣሊያን፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቱርክና ጃፓን ሊካተቱ እንደሚችሉ ተንታኞች ግምታቸውን አስቀምጠዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡