ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ገለጹ

የፌረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

የነዳጅ ዋጋ እና የኑሮ ውድነት ያስከተሉትን የኑሮ ጫና መቋቋም የተሳናቸው ፈረንሳዊያን የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስተዳደር ላይ ጥያቄዎችን አንግበው ወደ አደባባይ ወጥተው ብሶታቸውን ማስተጋባት ከጀመሩ አራት ሳምንታት አስቆጥረዋል፡፡

በቴሌቭዥን መስከኮት ብቅ ብለው በኑራቸው ሁኔታ ለተከፉ ፈረንሳዊያን መልዕክት አለኝ ያሉት ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አመጹን በማውገዝ የተቃውሞው ስሜት ጥልቅና ህጋዊነትም የሚታይበት ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

ከቀናት በኋላ በሚጀመረው የፈረንጆቹ አዲስ አመት ትንሹ የላብ ክፍያ የአንድ መቶ ዩሮ ጭማሬ ይኖረዋል ሲሉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ መንግስታቸው በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ሰዎች ላይ ሊኖር የሚችለውን የግብር ጫና እንደሚያስቀሩም ቃል ገብተዋል፡፡ 

በትርፍ ጊዜ ሥራ ላይ ይከፈል የነበረው ግብር መቅረቱን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ አመታዊ ጉርሻዎችም ምንም ሳይቆራረጡ ከሠራተኛው እጅ ይገባሉ ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ያሳለፉት ውሳኔ የፈረንሳይን መንግስት ከስምንት እስከ አስር ቢሊየን ዩሮ ተጨማሪ በጀት እንዲይዝ ያስገድደዋል ተብሏል፡፡

በፈረንሳይ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለማርገብ የፕሬዝዳንት ማክሮን አስተዳደር ይህን ውሳኔ ከማሳለፍ ውጭ ሌላ አማራጭ እንዳልነበረው ተንታኞች ያብራራሉ፡፡

ፈረንሳዊያን ከፖለቲካዊ ቃል ባለፈ የሚጨበጥ እርምጃ ከመንግስታቸው ይጠብቃሉ የሚሉት ተንታኞች ይህ ደግሞ ኪሳቸው በሚገባው ገንዘብ እንደሚለካም ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ የፕሬዝዳንት ማክሮን አስተዳዳር የወሰዷቸው እርምጃዎች ከዚህ አንጻር በፈረንሳይ አዲስ ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት መንገዱን የሚያመቻች መሆኑን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኞቹ ለቢቢሲ በሠጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል፡፡

ከአራት ሳምንታት በፊት በፌስቡክ የተላለፈው የመጀመሪያ የተቃውሞ ሰልፍ ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝቶ መንግስትም ማሻሻያ እንዲያደርግ ያስገደደ ሆኗል፡፡

ፕሬዝዳንት ማክሮንም በተቃውሞው የተደመጡ ፍላጎቶችን ይቀበሏቸዋል፡፡ ባለፉት 40 አመታት የፈረንሳዊያን የኑሮ ሁኔታ እየከፋ በመምጣቱ ማህበራዊ ግንኙነታቸውም እየተሸረሸረ መጥቷል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡  

ዛሬም በፈረንሳይ ተገቢው እውቅና ያልተሠጣቸው የማህበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አጠቃላይ ስለሆነው ህዝብ ሲወራ ተረስተው የቆዩ በርካቶች ናቸው ሲሉ ተቃውሞውን እንዳልጠሉት በተዘዋዋሪ አመላክተዋል፡፡ 

በተናገርኩት ሁሉ ቅድሚያ የሰጥኋቸው ጉዳዮች ሌሎች በመሆናቸው ሳስቀይማችሁ የነበራችሁ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳላችሁ እረዳለሁም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡

ማክሮን የታችኛውን የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎት እንደሚያሻሽሉ ቃል ገብተው ለጠንካራ ሀገራዊ አንድነት ሁሉም መስራት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የተቃውሞው ተሳታፊዎች በማክሮን ውሳኔ መደሰታቸውን ገልጸው ከጥያቄዎቻቸው የተመለሱት ጥቂቶቹ በመሆናቸው በሰፊው እንጠብቃለን ብለዋል፡፡

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞው እንደሚቀጥልና የተወሰደው እርምጃ ተቃውሞውን ለማቃለል እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመፍጠር አይደለም ሲሉ ማክሮን የሰራቸውን ስህተቶች በሙሉ ማረም ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ዬለው ቬስት የተሰኘው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በቢጫ የስራ ላይ ሰደሪያ የተሰየመበት ምክንያት ደምቆ ለመታየት ያስችላል ተብሎ በመታመኑ ነው፡፡

በነዳጅ ላይ የተጣለው ከፍተኛ ግብር ያስቆጣቸው ተቃዋሚዎች ከነመኪኖቻቸው አደባባይ በመውጣት ተቃውሞውን ለማካሄድ ሲያበቃቸው ታዳሽ ሀይልን መጠቀምን ለማበረታታት የተወሰደው እርምጃ ፕሬዝዳንት ማክሮንን ደግሞ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ከቷቸዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ተቃዋሚዎቹ የተያያዘ ሌሎች ብሶቶች በተቃውሟቸው አሰምተዋል፡፡ የተሻለ ደመውዝ፣ የተሻለ የኑሮ ሁኔታ፣ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ መስፈርቶችን ማቅለል ከተነሱ ጥያቆዎች ከብዙ በጥቂቱ የተገለጹት ናቸው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡