የኢራኑ ፕሬዚደንት ሃሰን ሮሃኒ በአዲሱ ዓመት የመንግሥትን አጠቃላይ በጀት ለፓርላማ አቀረቡ

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሃኒ የአዲሱ አመት የሀገሪቱ አጠቃላይ በጀት 4700 ትሪሊየን ሪያል ወይም 47 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር እንዲሆን ለፓርላማቸው አቅርበዋል፡፡

ይህ በጀት አሜሪካ በኢራን ላይ ያስተላለፈችው የኢኮኖሚ ማዕቀብ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ታሳቢ ተደርጎ የቀረበ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ግንቦት ወር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸውን ከአለም አቀፉ የኢራን የኒውክሌር ስምምነት ማስወጣታቸውን ተከትሎ አሜሪካ በኢራን ላይ ዳግም የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣሏ አይዘነጋም፡፡

ይህ ማዕቀብ በተለይም የሀገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነውን የነዳጅ ሀብት የሚያካትት በመሆኑ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሚሆን ይነገራል፡፡

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሃኒ የመጪው አዲስ አመት የሀገሪቱ አጠቃላይ በጀት 4700 ትሪሊየን ሪያል ወይም 47 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንዲሆን ለፓርላማቸው አቅርበዋል፡፡

አሜሪካ በሀገራቸው ላይ የጣለችው የኢኮኖሚ ማዕቀብ የዜጎቻቸውን ኑሮና የኢኮኖሚ አቅም እንደሚጎዳ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ ይህ ማዕቀብ ግን የመንግስታችንን ጉልበት አያንበረክከው ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሮሀኒ የአዲሱን አመት በጀት ረቂቅ ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት የአሜሪካ አላማ የኢራንን እስላማዊ ስርአት ማንበርከክ መሆኑን ገልጸው÷ ይህ አላማቸው ግን ፈጽሞ ሊሳካላቸው አይችልም ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም አሜሪካ በኢራን ላይ ያስተላለፈችው ማዕቀብ  የዜጎች ህይወት እና የአገሪቱ የልማት እና የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ጥርጥር የለውም ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ አዲሱ በጀት ይህን ተጽዕኖ ለመቋቋም ያስችለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሮሃኒ የቀረበው በጀት ተከትሎ የመንግስት ሰራተኞች በሀያ በመቶ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በጀቱ ምግብና መድሀኒትን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶችን ለዜጎች በድጎማ መልኩ ለማቅረብ የሚያስችል 14 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር አካቶ እንደያዘም ተናግረዋል፡፡

ይህ የድጎማ ገንዘብ ከያዝነው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የአንድ ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡

የሀገሪቱ ባለስልጣናትም በጀቱ የመንግስት ሰራተኞችንና ጡረተኞችን ጨምሮ ዝቅተኛ ገቢ ላቸው የሀገሪቱ ዜጎች መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ለማቅረብ ታሳቢ ተደርጎ የቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጀቱ ምርታማነትን ለማሳደግና የስራ አጥነትን ለመቀነስ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል፡፡

አሁን ላይ ቆመው የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ፕሮጀክቶችንም በግል ባለሀብቶች እገዛ ለማስጀመር እገዛው የጎላ እንደሚሆን ይጠበቃል ሲል ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡