የአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ኩባንያ ጥያቄዎች እየቀረቡበት ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 ትናንት ማለዳ 157 ሰዎችን ይዞ መከስከሱን ተከትሎ የአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ኩባንያ ጥያቄዎች እየቀረቡበት ይገኛሉ።

ቦይንግ ጥያቄዎች የቀረቡበት ትናንት በበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ላይ ከደረሰው አደጋ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ክስተት የላይን ኤየር ንብረት የሆነ ቦይንግ 737 አውሮፕላን በጥቅምት ወር ኢንዶኔዥያ ላይ 189 ሰዎችን ይዞ በመከስከሱ ነው ተብሏል።

ይህንን ተከትሎ ታዲያ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቻይና የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ቦይንግ 737-8 ማክስ የተሰኙት አውሮፕላኖች በጊዜያዊነት ከበረራ ማገዳቸው ተሰምቷል።

በርግጥ በዘርፉ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች የአደጋው መንስዔ ባልታወቀበት ሁኔታ እርምጃው የፈጠነ ነው እያሉ ቢገኙም ገበያውን በቅርቡ የተቀላቀለው አዲሱ ቦይንግ አውሮፕላን ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ መከስከሱ ጥያቄዎችን አስነስቷል።

አዲሱ የቦይንግ ምርት አውሮፕላን ከሚነሱበት ጥያቄዎች መካከልም ከሶፍትዌር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ዋነኛው ነው ተብሏል።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ቁመቱ 39 ነጥብ 52 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፥ ወደ ጎን ያለው ስፋት ደግሞ 35 ነጥብ 9 ሜትር ነው።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በጠቅላላ 210 መቀመጫዎች እንዳሉት መረጃዎች ያመለክታሉ። (ምንጭ፦ቢቢሲ)