አሜሪካ የቻይና ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ ልትጥል ነው

አሜሪካ 200 ቢሊየን ዶላር በሚያወጡ የቻይና ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ ልትጥል መሆኑን አስታወቀች።

ከፊታችን አርብ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል በተባለው በዚህ ውሳኔ ከ10 እስከ 25 በመቶ የሚደርስ ተጨማሪ ቀረጥ ነው የተጣለው ተብሏል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ እንደሚጥሉ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ዋሽንግተን ከቤጂንግ ጋር በምታደርገው የንግድ ድርድር ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚል ተጨማሪ ቀረጥ ለመጣል መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል። ይህንን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት በዚህ ሳምንት አጋማሽ በዋሽንግተን የንግድ ድርድር ሊያደርጉ እቅድ ይዘው ነበር።

ሆኖም የትራምፕ አስተያየት እመርታ እያሳየ በመጣው የሁለቱ ሃገራት የንግድ ድርድር ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል እየተባለ ነው።

ወል ስትሪት ጆርናል ደግሞ ቻይና ከትራምፕ አስተያየት በኋላ የዋሽንግተኑን ድርድር ለመሰረዝ ስለማሰቧ ሰኞ ዕለት ዘግቧል።

ቻይና ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን የንግድ ድርድር እንደምትቀጥል ማስታወቃቸውን ሽንዋ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይን ጠቅሶ አስነብቧል።

 (ምንጭ፦ ሪውተርስ)