አሜሪካ የቀረጥ ጭማሪ ማድረጓን እንድታቆም ቻይና አስጠነቀቀች

ቻይና እና አሜሪካ የገቡበት የንግድ ጦርነት መፍትሄ እስኪበጅለት ድረስ አሜሪካ የቀረጥ ጭማሪ ማድረጓን እንድታቆም ቻይና አስጠነቀቀች፡፡

የቻይናዉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የሀገሪቱ ከፍተኛ የንግድ ተደራዳሪ ሊዉ ሂ ሁለቱ ሀገራት ለገቡበት የንግድ ዉዝግብ አንዳች ስምምነት ሳይፈፅሙ አሜሪካ ከቻይና በምታስገባቸዉ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ መጣሏ ተገቢ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በለፈው አርብ እለት በዋሺንግተን ዲሲ የተካሄደዉንና በሁለቱ ሀገራት ወቅታዉዊ የንግድ ግንኙነት ላይ የመከረዉን ዉይይት ካጠናቀቀቁ በኋላ ለሀገራቸዉ ብዙሀን መገናኛዎች በሰጡት መግለጫ ነው ይህን የተናገሩት።

በዉይይት የሁለቱም ሀገራት ተደራዳሪዎች የጋራ አቋም መያዝ ተስኗቸዉ ያለ ስምምነት መለያየታቸዉም ነው የተገለጸው።

የሲኤንኤን ዘገባ እንዳመላከተዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም የቀረጥ ጭማሪ ባልተደረገባቸዉ የቻይና ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ የመጣሉ ሂደት እንዲጀመር ለሀገራቸዉ የንግድ ተደራዳሪ ሮበርት ላይትዘር ትዕዛዝ ማስተላለፋቸዉ ተሰምቷል።

ተጨማሪ ቀረጡ 3መቶ ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በሚገመት የምርት መጠን ላይ የሚጣል ስለመሆኑም ተነግሯል።

የቻይናዉ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዉ ሂም ሀገራቱ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍን አንዳች ስምምነት እስኪፈራረሙ ድረስ አሜሪካ ተመሳሳይ የታሪፍ ጭማሪ ከማድረግ እንድትቆጠብ ጠይቀዋል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገዉ የንግድ ድርድር በቤጂንግ እንደሚቀጥል የገለፁት የቻይናዉ ተደራዳሪ ሊዉ ሂ ፣ የቤጂንጉ ድርድር የተሻለ መግባባት የሚፈጠርበት እንደሚሆንም ተስፋ አድርገዋል።