የአሜሪካ እና ቻይና የንግድ ጦርነት በዓመታዊ ገቢያቸው ላይ አሉተዊ ተፅእኖ መፍጠሩ ተገለጸ

የአሜሪካ እና የቻይና የንግድ ጦርነት በሁለቱ ሀገራት ዓመታዊ ገቢ ላይ አሉተዊ ተፅእኖ መፍጠሩ ተገለጸ፡፡

አሜሪካ ወደ ሃገሯ የምታስገባቸው የቻይና ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ ካደረገች በኋላ ከቻይና ጋር የንግ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ የሁለቱ ሀገራት ፍጥጫ ከራሳቸው አልፎ በሌሎች ሃገራት ላይ ተፅእኖ መፍጠሩ አልቀረም፡፡

ዋና መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት እና የፋይናንስ ባንክ ጄፒ ሞርጋን በ40 ሃገራት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፤ ሀገራቱ በገቡበት የንግድ ጦርነት ያስከተለውን አሉታዊ ተጽእኖ አስመልክቶ ጥናቶች ማድረጉን ይገልጻል፡፡

ባንኩ ባወጣው መረጃ መሰረትም በአሜሪካ እና በቻይና መካከል የተፈጠረው የንግድ እሰጣ ገባ በሁለቱም ሃገራት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ መሆኑን የቻይና ኢኮኖሚ ባለሞያ እና በቻይና የጄፒ ሞርጋን የሰትራቴጂ ክፍል ሃላፊ ዙ ሃቢን ገልጸዋል፡፡

አሜሪካ 200 ቢሊየን ዶላር በሚያወጡ የቻይና ምርቶች ላይ ከ10 እስከ 25 በመተ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጓን ተከትሎ የቻይና ዓመታዊ ምርት እድገት በአውሮፓዊያኑ 2019 እና በ2020   በ0.4 በመቶ ብቻ ይሆናል ተብሏል፡፡ 

በአሜሪካ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ተፅእኖ ደግሞ በ0.2 በመቶ ሊሆን እደሚችል ጥናቱ የጠቆመ ሲሆን የዋጋ ግሽበቱ ግን እየጨመረ እንደሚሄድ አመላክቷል፡፡ ይህ ሁኔታ የንግድ ጦርነቱ ለሁለቱም ሀገራት የኢኮኖሚ ሽንፈትን የሚያጎናፅፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ ቻይና በፈረንጆቹ 2019 በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሀገራዊ የምርት እድገቷ 6.4 በመቶ ሲሆን የአሜሪካ ምርት ዕድገት ደግሞ 3.2 በመቶ ሆኗል፡፡

አሜሪካ እና ቻይና ኢኮኖሚያቸው ላይ በንግድ ጦርነቱ አማካኝነት የሚፈጠረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመፍታት የሁለቱ ሀገራት አመራሮች በምክንያታዊ አስተሳሰብ ሊወያዩ እደሚገባ የጂ ፒ ሞርጋን ሪፖርት ማተቱን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡