ህንድ በተለያዩ የአሜሪካ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ ልትጥል ነው

ህንድ የለውዝና የአፕል ምርቶችን ጨምሮ በ28 የአሜሪካ ሸቀጦች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ ልትጥል መሆኑን አስታውቃለች፡፡

ይህም አሜሪካ በህንድ ብረታ ብረትና አሉሙኒየም ምርቶች ላይ ለምትጥለው ከፍተኛ ቀረጥ አፃፋዊ ምላሽ የሚሆን ነው ተብሏል፡፡

አዲሱ ታሪፍም ከእሁድ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን የሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው በንግዱ ዘርፍ ለህንድ የምታደርጋቸውን የተለያዩ ድጎማዎች እንደምታቆም መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

ይህን ተከትሎም ህንድ ባለፈው ዓመት እስከ 120 በመቶ የሚደርስ ታሪፍ በአሜሪካ ምርቶች ለመጨመር አቅዳው የነበረውንና በተለያዩ ምክንያቶች የዘገየውን ውሳኔ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲባል ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

የአሜሪካና የህንድ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ በባለፈው አመት 142 ቢሊየን ዶላር የነበረ ሲሆን፥ ይህም 17 ዓመት በፊት ከነበረው ቁጥር ጋር ሲወዳደር ሰባት እጥፍ  ያህል ጨምሯል ነው የተባለው፡፡

(ምንጭ፦ቢቢሲ)