ባራክ ኦባማ አሜሪካውያን ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን እንዲያስጠብቁ ጠየቁ

ፕሬዚዳንት ኦባማ በቺካጎ የስንብት ንግግራቸውን ሲያደርጉ አሜሪካውያን ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ እንዲመለከቱ እና የመደማመጥ ባህላቸውንም እንዲያስቀጥሉ ጠየቁ።

ከስምንት ዓመት በፊት ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ከነበረችው አሜሪካ የአሁኗ “በየትኛውም መመዘኛ የተሻለች እና ጠንካራ ናት” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ ።

ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የአሜሪካ ዴሞክራሲ ልዩ ምልክት መሆኑን ጠቁመዋል።

ፍትሃዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል፣ የዘር ክፍፍል እና በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ አስተያየት የሀገሪቱ ዴሞክራሲ ስጋቶች መሆናቸውንም አንስተዋል።

በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት የረዷቸውን ወጣት አሜሪካውያን እና ማንኛውም በእኩልነት እና ሁሉን ተጠቃሚ የምታደርግ አሜሪካ እንድትፈጠር የሚተጉ ዜጎች ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ከነበራቸው በበለጠ ተስፈኛ እንዳደረጓቸውም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በዶናልድ ትራምፕ ለመተካት ጊዜው መቃረቡን ተከትሎ ሰጋት የገባቸው በቺካጎ የተሰባሰቡ ደጋፊዎቻቸው ኦባማን ለሌሎች አራት አመታት ዋሽንግተንን ቢመሩስ የሚል ጥያቄ አቅርበው “ይህን ማድረግ አልችልም፤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ አይፈቅድም” ብለዋቸዋል።

ኦባማ በመዝጊያ ንግግራቸው በፕሬዚዳንታዊ ስልጣኔ አሜሪካውያንን በመጨረሻ የምጠይቀው “እኔ ለውጥ ለማምጣት ባለኝ አቅም ሳይሆን በራሳችሁ እንድትተማመኑ” ነው ብለዋል።

በዋይት ሀውስ የስንብት ንግግራቸውን የሚያደርጉት ቀዳማዊ እመቤት ሚሸል ኦባማንም አሞካሽተዋል።

የ55 አመቱ የአሜሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በ2008 ሀገሪቱን እንዲመሩ ሲመረጡ በተስፋ እና ለውጥ የተሞሉ መልዕክቶችን ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ኦባማ በ2008 44ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ ድላቸውን ባበሰሩባት ቺካጎ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት ያደረጉት ንግግር አዎንታዊ መልዕክቶች የተላለፉበት ነው ተብሏል።

ተከታያቸው ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የኦባማ አሻራ ያረፈባቸውን የተወሰኑ ፖሊሲዎች እስርዛለሁ ብለዋል።

ከ10 ቀናት በኋላም ቃለ መሃላ ፈፅመው በይፋ ሀገሪቱን መምራት ይጀምራሉ-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።