የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሮሀኒ ያለንበት ዘመን በሀገራት መካከል የድንበር አጥር የሚገነባበት አይደለም ብለዋል፡፡
ሮሃኒ ይህን ያስገነዘቡት በ17ኛው የዓለም የአስጎብኚዎች ማህበራት ኮንፍረንስ በቴህራን በተደረገበት ወቅት ነው፡፡
"ከዓመታት በፊት የበርሊን ግንብ መፍረሱን ረሱት እንዴ?" ሲሉ አሜሪካውያን መሪዎች በሜክሲኮ ድንበር ሊገነቡ ያቀዱትን የግንብ አጥር ኮንነዋል፡፡
በሀገራት መካከል አስቀድሞ የተገነባ አጥር ቢኖር እንኳ ሊፈርስ እንደሚገባው ነው ሮሃኒ የገለጹት ፡፡
ዘመኑ አንድ ሀገር ከሌላው ሀገር ወይም ህዝብ ከህዝብ በድንበር አጥሮች የሚራራቅበት ጊዜ አለመሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል፡፡
የመተባበር እና የመልካም ጉርብትና ዘመን ነው ላይ ነው ያለነው ብለዋል ፡፡
ሮሃኒ በባህል፣ በሳይንስ፣ በስልጣኔ መንገዶች፣ እንዲሁም በዓለም አቀፋዊ የመግባቢያ መንገዶች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተሳሰርንበት ዘመን በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
ግሎባላይዜሽንን ማንም ማስቆም እንደማይችል ያመለከቱት የኢራኑ መሪ የሀገራት መቀራረብም በእነዚህ መንገዶች እውን መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
ኢራን ለሰላማዊ ጉርብትና እና ለእርቅ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ አላት በዚህም የጋራ ሰላምን የሚያመጣ ስርዓትን ለዓለም ለማምጣት ከሀገራት ጋር እንደምትሰራም ነው ያስገነዘቡት፡፡
አሁን ዓለምን እያስጨነቃት ያለው ሽብርተኝነት የቀድሞ ስልጣኔዋን እያወደመ ሲሆን ጥፋቶችን እያስከተለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ኢራቅ እና ሶሪያ ለሚያደርጉት የፀረ- ሽብር ዘመቻም ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል፡፡
በኮንፍረንሱ ላይ ለመሳተፍ ከ40 በላይ የዓለም ሀገራት በስፍራው ተገኝተዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)፡፡