ዩናይትድ ስቴትስ ለኔቶ ድጋፏን እንደምታጠናክር ገለጸች

ዩናይትድ ስቴትስ ለምትመራዉ ለሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የምትሰጠዉን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምትቀጥል አዲሱ የሐገሪቱ መከላከያ ሚንስትር አረጋገጡ።

መከላከያ ሚንስትር ጄምስ ማቲስ ዛሬ ብራስልስ-ቤልጂግ ዉስጥ ለተቀሩት የኔቶ አባል ሐገራት መከላከያ ሚንስትሮች እንደነገሩት የጦር ተሻራኪዎቹ ድርጅት ለአሜሪካም ሆነ ለተቀሩት አባላቱ በሙሉ የማዕዘን ድንጋይ ነዉ።«በጋራ ለመቆም በመወሰናችን፤ ሽርክናዉ ለዩናይትድ ስቴትስም ሆነ ባጠቀላይ ለአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ማሕበረሰብ ጠንካራ መሠረት ነዉ።

ፕሬዝደንት ትራምፕ እንዳሉት ለኔቶ ጠንካራ ድጋፍ ያደርጋሉ።ኔቶ ደግሞ በለዉጥ ሒደት ላይ ነዉ። የሚያጋጥሙትን የፀጥታ ፈተናዎች ለመቋቋም እራሱን ማስተካከል አለበት።ይሕ አዲስ ነገር አይደለም።የለዉጡ ሒደት ትንሽ አዝግሞ ይሆናል።ግን ይሕን ማስወገድ አይገደንም።

ፍፁም አስፈላጊም ነዉ።አንድ የአዉሮጳ መከላከያ ሚንስትር ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ከዓለም እጅግ ምርጥ የሆነዉን የመከላከያ ጥቅም የሚያገኙ በሙሉ፤ ነፃነትን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስፈልገዉን ወጪ እንዲጋሩ ቢጠየቁ ተገቢ ጥያቄ ነዉ።አንድ መርሳት የሌለብን ነገር እኛ በኔቶ አማካይነት ከጥቃት የምንከላከለዉ ነፃነትን መሆኑን ነዉ።»

አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት ኔቶን «ያረጃ» እና ለአሜሪካ «ሸክም ነዉ» ማለታቸዉ አዉሮፓዉያንን  ክፉኛ አስደንግጦ ነበር።መከላከያ ሚንስትር ጄምስ ማቲስ ዛሬ ከአዉሮጳ አቻዎቻቸዉ ጋር ያደረጉት ስብሰባ በትራምፕ መልዕክት የተደናገጡትን መንግስታት ለማረጋጋት ያለመ ነዉ።

የቀድሞዉ ጄኔራል ከአዉሮጳ መከላከያ ሚንስትሮች ጋር በግልፅ ለመነጋገር እና የሌሎቹን ሐሳብ ለመስማት ዝግጁ መሆናቸዉንም አስታዉቀዋል። (www.dw.com)