ዩናይትድ ስቴትስ እና የሩሲያ ግንኙነት ሊሻሻል እንደሚችል የሁለቱ ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች አስታወቁ። እዚሕ ቦን ከተደረገዉ የቡድን 20 አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባ ጎን የተወያዩት የሁለቱ ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች እንዳስታወቁት ሞስኮና ዋሽግተን በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተባብረዉ ይሰራሉ።
የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ «አርቴፊሻል» ያሉትን የሁለቱን ሐገራት ጠብ ለማስወገድ ዋሽግተኖች እንደሚጥሩ የአሜሪካዉ አቻቸዉ አረጋግጠዉላቸዋል። «በኦባማ መስተዳድር በተለይም በመጨረሻዎቹ ወራት ክፉኛ ሥለተበላሸዉ ሥለሁለቱ ሐገራት ግንኙነት ተነጋግረናል።ፕሬዝደንት ትራምፕ ያንን ችግር ለማቃለልና ግንኙነታችንን የሚያጉለዉን (አርቴፊሻል) እንቅፋት ለማስወገድ እንደሚፈልጉ ሬክስ ቲለርሰን አረጋግጠዉልኛል።»
የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርም መስተዳድራቸዉ ከሩሲያ ጋር ተባብሮ መስራት እንደሚፈልግ አረጋግጠዋል።የቀድሞዉ የነዳጅ አምራች ኩባንያ ሥራ-አስኪያጅ ቲለርሰን እንደሚሉት ጥቅም ካለ ፤ ትብብር አለ።«በሴኔቱ የሹመት ማረጋገጪያዬ ወቅት ግልፅ እንዳደረግሁት፤ የአሜሪካን ሕዝብ እስከጠቀመ ድረስ ፣ አሜሪካ፣ ከሩሲያ ጋር ተባብራ የምንሰራበት መስክ ሲገኝ፣ አብረን የምንሰራበት ሁኔታን ታጤናለች። ፊት ለፊት በማንተያይበትም፤ ዩናይትድ ስቴትስ የአሜሪካ እና የተባባሪዎችዋ ጥቅምና እሴትን ለማስጠበቅ ትቆማለች።»
ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቲለርሰን የቦኑን ስብሰባ የሐገራቸዉንና የቻይናን ጠብ ለማርገብም ተጠቅመዉበታል።ፕሬዝደንት ትራምፕ «አዲት ቻይና» የሚለዉን የቤጂንግን ነባር ዓላማን የሚፃረር አስተያየት በመስጠቸዉ ቻይኖች ተቆጥተዉ ነበር።የቻይናዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ሊም የአሜሪካ አቻቸዉን ላለማነጋገር ሲሉ በቦኑ ስብሰባ እንደማይገኙ አስታዉቀዉ ነበር።ዊንግ ወደ ቦን የመጡት፤ ትራምፕ ለቻይናዉ ፕሬዝደንት ለዢ ቺ ጂንፒንግ ሥልክ ደዉለዉ የሰጡትን አስተያየት መሳባቸዉን ከገለፁ በኋላ ነዉ።ቲለርሰን የቻይናዉን አቻቸዉን ትናንት ባነጋገሩበት ወቅትም ዋሽግተን የቤጂንግን መርሕ እንዳማትፃረር አረጋግጠዉላቸዋል። (www.dw.com)