ትራምፕ የ6 አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ያወጡት ክልከላ እንዳይፈፀም የተጣለው ገደብ እንዲራዘም ተወሰነ፡፡
በሃዋይ የሚገኝ የዩናይትድ ስቴትስ ፌደራል ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስድስት አገራት ዜጎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ለሁለተኛ ጊዜ አውጥተው የነበረው ክልከላ እንዳይፈፀም የጣለው ገደብ እንዲራዘም ወሰነ።
ፍርድ ቤቱ የእግድ ማመልከቻውን ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው የሃዋይ አቃቤ ህግ እና በፌደራሉ መንግስት ፍትህ ቢሮ መካከል የተካሄደውን ክርክር አድምጦ ነው ውሳኔውን ያሳለፈው።
ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆቹ መጋቢት 5 ላይ ፕሬዚዳንታዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ከሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ሶሪያ እና ኢራን ለ90 ቀናት ሰዎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ እንዲሁም፥ የእነዚህ አገራት ስደተኞች ለ120 ቀን እንዳይገቡ አግደው ነበር።
ፍርድ ቤቱ የፕሬዚዳንት ትራምፕ እገዳ ለቱሪዝም፣ የውጭ አገራት ተማሪዎችን ለመቀበል እና ሰራተኞችን ለመቅጠር አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል በሚል ነው በፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ተፈፃሚነት ላይ የጣለውን ገደብ ላልተወሰነ ጊዜ ያራዘመው።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እገዳውን ያወጡት አገራቸውን ከአሸባሪዎች ስጋት ነፃ ለማድረግ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።