በሩሲያ በባቡር ጣቢያ ላይ ጥቃት ያደረሰው ግለሰብ ማንነት ታወቀ

በሩሲያ ቅዱስ ፒተርስበርግ በምድር ውስጥ የባቡር ጣቢያ ላይ ጥቃት ያደረሰው ግለሰብ ትውልደ ኪርጊስታናዊ ነው ተብሏል፡፡

የማዕከላዊ እስያዊቷ ሀገር የፀጥታ አገልግሎት እንዳስታወቀው፥ የፍንዳታ ጥቃቱን የፈፀመው ተጠርጣሪ የተለየ ሲሆን የኪርጊስታን ተወላጅ ሆኖ የሩሲያ ዜግነትን ያገኘ ግለሰብ ነው፡፡

ሲኤን ኤን ባወጣው መረጃ የጥቃት አድራሹ ስም አክባርጆን ጃሊሎቭ  ነው የሚባለው፡፡

በሁለት የምድር ውስጥ ባቡር ጣያዎች በተከሰተው ፍንዳታ ከሞቱት 14 ሰዎች በተጨማሪ እንደ ሩሲያ ቴሌቪዥን መረጃ ከሆነ ከ51የማያንሱ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ህክምና ተቋማት ተወስደዋል፡፡

ጥቃት አድራሹ አጥፍቶ ጠፊ በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ መሆኑ በርካቶችን እያነጋገረ ነው፡፡

የኪርጊስታን የፀጥታ አገልግሎት ከሩሲያ የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ተጨማሪ ምርመራዎችን እንደሚያደርግ ነው የጠቀሰው፡፡

የቦምብ ፍንዳታውን ያደረሰው የ23 ዓመቱ ትውልደ ኪርጊስታናዊ ወጣት ከፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ቢገመትም በጥቃቱ ራሱን አጥፍቷል፡፡

ሆኖም በሌላ የባቡር ጣቢያ ተመሳሳይ ጉዳት ሊደርስ የሚችል ዓይነቱ ያልታወቀ የቦምብ ስሪት ተጠቀምዶ መገኘቱ አንዲት ሴት ጥቃቱን በማድረስ ከወጣቱ ጋር ተባባሪ ነበረች የሚል ግምት እንዲሰጥም ማድረጉ ነው የተጠቆመው፡፡

የሟቾች ቁጥር 14 የደረሰ ሲሆን ለጥቃቱ እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን አለመኖሩ ተጠቁሟል፡፡

ሩሲያ በዜጎቿ ሞት እና ጉዳት የተሰማትን ሀዘን ለመግለፅ የሶስት ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን አውጃለች፡፡

ታስ እና ኢንተርፋክስ የተሰኙ የሩሲያ የዜና ወኪሎችን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፥ ፍንዳታው ሳንያ ፕሎሽቻድ የተሰኘ የባቡር ጣቢያ ላይ ነው የደረሰው።

ፑቲን ትናንት በትውልድ ከተማቸው በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ በነበሩበት ወቅት ነው ጥቃቱ የደረሰው፡፡

የሩሲያ የመገናኛ ብዙሃን በሳንያ ፕሎሽቻድ ባቡር ጣቢያ ውስጥ ከደረሰው ፍንዳታ በኋላ በአቅራቢያው በሚገኝ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባቡር ጣቢያ ተመሳሳይ የፍንዳታ ሙከራ መድረሱን ዘግበዋል፡፡

ይህን ፍንዳታ ተከትሎም የሞስኮ ባቡር ጣቢያዎች የደህንነት ጥበቃቸውን ማጠናከራቸው ተሰምቷል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቅዱስ ፒተርስበርግ ጥቃትን ተከትሎ ለፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስልክ ደውለው አደጋው አሳዛኝ መሆኑን በመጥቀስ ሽብርተኝነት መወገድ እንዳለበት ተነጋግረዋል-(ኤፍ ቢ ሲ)፡፡