አሜሪካ የጦር መርከቦቿን ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር አሰማራች

የአሜሪካ መከላከያ የባህር ኃይሉን ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር እንዲሰማራ አዟል።

ዋሽንግተን ይህን ትዕዛዝ ያሳለፈችው የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ፕሮግራም አሳስቦኛል በማለት ነው።

ግዙፏ የአሜሪካ ባህር ሀይል አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ “ካርል ቪንሰን” እና ሌሎች የጦር መርከቦች ናቸው ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር እንዲሰማሩ የተደረገው።

በፓስፊክ የአሜሪካ ጦር ሀይሎች አዛዥ እንደገለጸው፤ ካርል ቪንሰን እና ሌሎች የተሰማሩት የጦር መርከቦች በአሁኑ ወቅት ወደ ምዕራባዊ ፓስፊክ እያመሩ ነው። 

የጦር መርከቦቹን ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር ማሰማራት ያስፈለገው የፒዮንግያንግን እንቅስቃሴ በቅርብ ርቀት ሆኖ ለመከታተል መሆኑን አስታውቋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምንም አይነት የሚሳኤል ወይንም ኒዩክሌር ሙከራ እንዳታደርግ ማዕቀብ የተጣለባት ሰሜን ኮሪያ፤ ባለፈው ሳምንት ከምስራቃዊ ሲንፖ ወደብ ወደ ጃፓን የባህር ክልል የባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏ የሚታወስ ነው።

አሜሪካም ይህ የፒዮንግያንግ ተደጋጋሚ የሚሳኤል እና ኒዩክሌር ሙከራ እንደሚያሳስባት ስትገልፅ ቆይታለች።

የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቴለርሰንም ወደ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና ቻይና ጉብኝት በማድረግ የፒዮንግያንግን የኒዩክሌር ፕሮግራም እንዴት መግታት ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ መክረዋል።

ከሰሞኑ ወደ አሜሪካ ያመሩት የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግም ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር በፒዮንግያንግ የኒዩክሌር ፕሮግራም ዙሪያ ተወያይተዋል።

በዚህ ውይይት ቻይና የቀጠናውን ውጥረት ለመቀነስ እንድትሰራ ከዋሽንግተን ጫና ቢደረግባትም ታሪካዊ ወዳጇን ማግለል አልፈቀደችም።

የፒዮንግያንግ ውድቀት ከፍተኛ የስደተኞች ቀውስ የሚያስከትል መሆኑንም ለዚህ በምክንያትነት ጠቅሳለች።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሺ ጂንፒንግ ጋር ካደረጉት ውይይት በፊት ቻይና “ችግር ፈጣሪ ጎረቤቷን” የማታስቆም ከሆነ አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን የኒዩክሌር ፕሮግራም ስጋትነት በራሷ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን መግለፃቸው ይታወሳል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።