ኢራን ከፀብ አጫሪነት ትንኮሳዋ እንድትታቀብ አሜሪካ አስጠነቀቀች

ቴህራን የሰሜን ኮርያን መንገድ በመከተል ከጀመረችው የፀብ አጫሪነት ትንኮሳዋ እንድትታቀብ  ዋሽንግተን አስጠነቀቀች   ፡፡

የቴህራን እንቅስቃሴ የማይጥማት ዋሽንግተን አሁንም የማስጠንቀቂያ መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡  የአሜሪካ መልዕክት ኢራን የመካከለኛውን ምስራቅ ለማተራመስ የጀመረችውን ጥረት እንድታቆም የሚያገነዝብ እንደሆነ ነው የተገለፀው፡፡

ኢራን መካከለኛውን ምስራቅ በማተራመስ በቀጣናው ሠላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን የጀመረችውን ጉዞ እንድታቆም አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስጠንቅቃለች፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ኢራን የመካከለኛውን ምስራቅ የማተራመስ ዋናው ግብ ዋሽንግተን በቀጣናው የሚኖራትን ጥቅም ማዳከምና ማስቆምን ያለመ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ኢራን አሜሪካ በኢራቅ፣ በሶርያ፣ በሊባኖስና በየመን ላይ ሊኖራት የሚችለውን ጥቅም ለመቀነስና ለማስቆም እየዶለተች መሆኑን ሚኒስትሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ኢራን የሰሜን ኮርያን ፈለግ በመከተል ዓለም ከጎንዋ እንዲሰለፍ እየጣረች መሆኑን ጠቁመው ከሠላም ይልቅ የጥፋት መንገድን ምርጫዋ ማድረጉ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

ኢራን በኢራቅና በየመን ሠላምና ፀጥታ እንዳይሰፍን የበኩሏን ጥረትና ድጋፍ ማድረጓንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እስራኤልን ለማዳከምና ለማጥቃት ኢራን የምትችለውን ሁሉ ከማድረግ አለመቆጠቧን ቲለርሰን ተናግረዋል፡፡

ለሀማስ ወታደራዊ ስልጠናና የገንዘብብ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ሌሎች በፍልስጥኤም ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ድርጅቶችን እየረዳች መቆየቷም አገሪቱ ከሠላም በተቃራኒ ለመሰለፏ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራም የኢራን የኒውክሌር ማበልፀግ ስምምነት ዳግም እንዲከለስ ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸውን ቢቢሲ ጠቁሟል፡፡

ኢራን በተደጋጋሚ ከምዕራባውያኑ ከኒውክሌር ማበልፀግ ጋር በተያያዘ የሚሰነዘርባትን ክስ እየተቃወመች ይገኛል፡፡

ፒዮንግያንግ በቅርቡ የሚሳኤል ሙከራ አድርጋ መክሸፉን  ተከትሎ  ዋሽንግተን ፒዮንግያንግ አንዳች ነገር እየዶለተች ነው ስትል ስጋቷን መግለፃ አይዘነጋም፡፡

ኢራንም የፒዮንግያንግን የጥፋት መንገድ ምርጫዋ ማድረጓ ለማንም እንደማይጠቅም አሜሪካ በጥብቅ ማሳሰቧን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ( ምንጭ  ቢቢሲ)