የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን እንዲለቁ የቀረበባቸውን ክስ ፍርድቤቱ ውድቅ አደረገው

የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ ከሙስና ጋር በተያያዘ ስልጣን እንዲለቁ የቀረበባቸውን ክስ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገው፡፡

በፈረንጆቹ 2015 አፈትልከው በወጡት የፓናማ ሰነዶች የተለያዩ መሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ተቋማትና ድርጅቶች ምስጢራዊ መረጃዎችን ይፋ ሆነዋል፡፡

ከእነዚህም የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ ስም ይጠቀሳል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሶስት ልጆች የሚያስተዳድሯቸው ተቋማት በዝርዝር ውስጥ መካተቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሸሪፍን ለክስ ዳርጓቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ቤተሰባቸው  ያልተገባ ሀብት እንዲያፈራ አድርገዋል በሚል ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡

በክሱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈፀሙት የሙስና ወንጀል ሥልጣናቸውን መልቀቅ እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ተቃውሞ ቀርቦባቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ቤተሰቦቻቸው በበኩላቸው የፈፀሙት ወንጀል እንደሌለ በመግለፅ ክሱን ተቃውመዋል፡፡

በቤተሰባቸው ስም የፈራው ሀብት በህጋዊ መንገድ የተገኘ እንደሆነም በመጠቆም፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ የቀረበውን ክስ ከተመለከተ በኋላ በቂ ማስረጃዎች ባለመቅረባቸው ክሱን ውድቅ አድርጎታል፡፡

ይህም ሆኖ ግን ከገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ምርምራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

 

ተጨማሪ ምርመራው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተሰቦች ስም በለንደን የተገዛው አፓርትመንት የገቢ ምንጩ ምን እንደሆነ ማጣራትን ያካትታል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተሰቦች ሀብት እንዴት ወደ ኳትር ሊዛወር እንደቻለም ይመረመራል ተብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሴት ልጃቸው ማሪያ ሸሪፍ በለንደን የተገዛው አፓርትመንት ወጭው በኳታር ከሚንቀሳቀስ የቤተሰቡ ድርጅት የተሸፈነ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉዳይ ለመመልከት የተሰየሙት አምስት ዳኞች የአቋም ልዩነት ማሳየታቸው በዘገባው ተመልክቷል፡፡

ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲከሰሱ የቀረበውን ሃሳብ ሲያጠናክሩ ሶስቱ ማስረጃው በቂ አይደለም በማለት ክሱን ውድቅ ማድረጋቸው ነው የተጠቆመው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሚገኝበት የአገሪቱ መዲና በሆነችው ኢስላማባድ በመገኘት ተቃውሞዋቸውን ማሰማታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ተቃዋሚዎቹ ‹‹ናዋዝ ይውረድ፣ናዋዝ ይበቃል›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ መጠየቃቸውን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡

ከአንድ ሺ 500 በላይ የፖሊስ አባላት ለደህንነት ሥራ ተሰማርተዋል፡፡

የፓናማ ሰነዶች ሞሳክ ፎንሴካ በተባለ የፓናማ የህግ ተቋም የተሰበሰቡ ምስጢራዊ ሰነዶች ናቸው፡፡

እነዚህ ሰነዶች ተቋሙ ባላወቀው መንገድ ማንነቱ ባልተገለፀ አካል ከአንድ የጀርመን ጋዜጠኛ እጅ መግባታቸውን ዘጋርድያን አስነብቧል፡፡

ይህን ተከትሎም በሰነዶቹ ውስጥ ስማቸው የተዘረዘሩ የአገር መሪዎችና ባለፀጋዎች ተጠያቂ እየሆኑ ነው፡፡

የፓናማ ሰነዶች 11 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ምስጢራዊ የፋይናንስና የሌሎች ሀብቶችን ዝርዝር መረጃዎች ይዘው የወጡ ናቸው ተብሏል ፡፡

ሰነዶቹ ከ214 ሺ 488 በሚበልጡ ተቋማትና ድርጅቶች ላይ የተጠናቀረ ዝርዝር መረጃዎችን መያዙንም ነው የተጠቆመው ፡፡