በፈረንሳይ በአንድ ተጣቂ የደረሰው ጥቃት ምርጫውን እንዳያስተጓጉል ተፈርቷል

በፈረንሳይ ትናንት በአንድ ታጣቂ የደረሰው ጥቃት  ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን እንዳያስተጓጉለው  መፈራቱ  ተገለጸ፡፡

አደጋውን ተከትሎ ምርጫው ሊራዘም ይችላል የሚል ስጋት እየተናፈሰ ነው፡፡ የፈረንሳይ መንግስት በበኩሉ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይካሄዳል ብሏል፡፡

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ሽርጉዱን የተያያዘችው ፈረንሳይ በጉዞዋ ላይ እንቅፋቶች እየተደቀኑ ያስቸገሯት ይመስላል፡፡ የምርጫ ፉክክሩ ከአሁኑ በችግሮች የታጀበ ነው የሚሉ በርካታ ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡ ምናልባትም ምርጫው ሳይራዘም አይቀርም የሚል አስተያያት የሚሠጡ  ሰዎች ይገኛሉ ።

ሰሞኑን በአገሪቱ አደጋ ለማድረስ በዝግጅት ላይ ነበሩ ያላቸውን ሁለት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፈረንሳይ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የምርጫ ሂደቱን ለማወክ አደጋ ለማድረስ እየተዘጋጁ  እንደነበር የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማቲያስ ፌክል ገልፀዋል፡፡

የወደብ ከተማ በሆነችው በደቡባዊ ማርስሌ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች የፈረንሳይ ዜጎች መሆናቸው ደግሞ አገሪቱ በፀጥታና ደህንነት ዙሪያ ትኩረት እንድትሰጥ ያሳሰበ መልዕክት ነው ተብሏል፡፡

ፈረንሳይ ቀደም ሲል የሽብር ጉዳይን ብዙም ትኩረት ሳትሰጠው ብትቆይም በተለይም እ.ኤ.አ በ2015 በፓሪስ የተከሰተው የሽብር ጥቃት ፊቷን ወደ ጠንካራ የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ እንድታዞር አድርጓታል፡፡

በትናንትው ዕለት  አንድ ታጣቂ በከፈተው ተኩስ  አንድ ፖሊስ በመግደል ሁለት ፖሊሶችን ካቆሰለ በኋላ  የፈረንሳይ  መንግሥት አስተማማኝ ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን እና ፀረ ሽብር ጉዞዋን ለማጠናከር የአስቸኳይ ጊዜ አውጃለች፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ እየተካሄደ ባለው የ2017 የምርጫ እንቅስቃሴ  ወቅት  በሻምስ  ኤሌዜ አደባባይ የደረሰው ጥቃት የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ እንዳያስተጓጉል ተፈርቷል ።

ከሽብርተኝነት ጋር ተያያዥነት አለው የተባለው አደጋ የፕሬዚዳንታዊ የምረጡኝ ቅስቀሳውን ላይ ትልቅ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን እየተነገረ ነው፡፡ የተወሰኑ ተፎካካሪዎች የምረጡኝ ቅስቀሳውን እንደሰረዙ በመጠቆም፡፡

በምርጫው የሚፎካከሩት 11 ተፎካካሪዎች ፕሮግራማቸውን በማስተዋወቅ የምረጡኝ ዘመቻ ላይ ባሉበት ወቅት የአደጋው ወሬ መሠማቱን ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡

ድርጊቱን የአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ፒዬሪ ሄንሪ ባንዴት እንዲህ በማለት ነበር ያስረዱት፡፡

‹‹አደጋ ያደረሰው ግለሰብ በመኪና እየመጣ የፖሊስ አውቶቡስ ወደ ቆመበት ቦታ ተጠጋ፡፡ አውቶማቲክ መሳሪያውን ይዞ ከመኪናው ወረደና የተኩስ እሩምታ አከታተለ፡፡ አንድ የፖሊስ መኮንን ገደለ፡፡ ወደ ሌሎች ፖሊሶች እየተኮሰ ለማምለጥ ባደረገው ሙከራ ሁለቱን አቆሰለ፡፡ ወዲያው በደህንነት ኃይሎች ተገደለ፡፡››

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ሆላንድ አደጋው ከሽብር ጋር የተያያዘ ለመሆኑ እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በአደጋው ህይወቱን ላጣው የፖሊስ አባልና ለቆሰሉት ሃዘናቸውን በመግለፅ፡፡

የፓሪስ አቃቤ ህግ ፍራንስዋ ሞሊንስ ከአደጋው በኋላ በሠጡት አጭር አስተያየት ‹‹አደጋውን ያደረሰው ግለሰብ ማንነት ታውቋል›› ብለዋል፡፡ ጉዳዩ በምርመራ ላይ በመሆኑም ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት መታቀብን መርጠዋል፡፡

የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን አደጋውን ያደረሰው ግለሰብ በሚሊኒየሙ መባቻ አካባቢ በፖሊስ ላይ ተኩስ በመክፈት ወንጀል ተከሶ ለብዙ ዓመታት በእስር ቤት ማሰለፉን እየዘገቡ ይገኛል፡፡

ፅንፈኛው አሸባሪ ድርጅት አይ ኤስ በበኩሉ አንድ የቡድኑ አባል አደጋውን ማድረሱን በመጠቆም ኃላፊነቱን መውሰዱ ተመልክቷል፡፡

ዕጩ ተፎካካሪዎቹ በደረሰው አደጋ ማዘናቸውን በመግለፅ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡

ቀኝ ዘመምዋ ማሪን ሌ ፔን የጥቃቱ ሰለባ በሆኑት የፖሊስ አባላት ላይ የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀው ከጎናቸው እንሰለፋለን ብለዋል፡፡ ግራ ዘመሙ ዕጩ ተወዳዳሪ ጄን ሉክ ሜሌንኮን በበኩላቸው በአደጋው ክፉኛ ማዘናቸውን ገልፀው የሽብር ጥቃትን ሁሌም እንዋጋለን ሲሉ ተደምጧል፡፡

አንዳንድ አካላት ከሽብር ጋር ተያያዥነት ያለው የሚመስለው አደጋ የምርጫውን ሂደት እንዳያጨልመው ስጋታቸውን እየገለፁ ነው፡፡ ምርጫው ሊራዘም ይችላል የሚሉም አልጠፉም፡፡

የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር በርናርድ ካዜኖውቬ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ  እንደሚከናወን በመግለፅ ስጋቱን አጣጥለዋል፡፡ ለዚህም መንግስት የፀጥታና ደህንት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስረዱት፡፡

አደጋውን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይና የጀርመኗን መራሂተ መንግስት አንጌላ ማርኬልን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች ኃዘናቸውን በመግለፅ ከፈረንሳይ ጎን እንደሚሰለፉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በተደጋጋሚ በአሸባሪዎች ጥቃት ክፉኛ የተጎዳችውና ከ230 በላይ ዜጎቿን ያጣችው ፈረንሳይ አሁንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ( ምንጭ: ቢቢሲ ፣ሲቢኤስ ኒውስ፣ ሲኤንኤን፣አልጀዚራና ሮይተርስ )