በፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመሃል ዘመሙና የቀኝ ፅንፈኛው ፓርቲ መሪዎች ለሁለተኛው ዙር አለፉ

በፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመሀል ዘመሙ ኢማኑኤል ማክሮንና የቀኝ ፅንፈኛው ፓርቲ መሪ ማሪን ለ ፔን  ለሁለተኛው ዙር አለፉ ። 

በ60 ዓመታት  የፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ታሪክ ውስጥ ዋነኞቹ የቀኝ ክንፍና የግራ ክንፍ ፓርቲ ተፎካካሪዎች ወደ ሁለተኛው  ዙር ያለፉበት ምርጫ ሆኖ ተመዝግቧል ።  

ባለፈው ሳምንት ከአሸባሪነት ጋር ግንኙነት አለው የተባለ ግለሰብ አንድ የፖሊስ መኮንንን ገድሎ፣ ሁለቱን አቁስሎ በደህንነት ኃይሎች መገደሉን ተከትሎ ድርጊቱ በፈረንሳይ ምርጫ ላይ እንቅፋት እንዳይሆን ፍራች  ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡

አሸባሪነት ምርጫዋን እንዳያስተጓጉለው ሰግታ የነበረቺው ፈረንሳይ ትናንት የመጀመሪያውን ዙር  ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በሠላም አጠናቅቃለች፡፡

በምርጫው ከተፎካከሩት 11 ዕጩዎችም ለሁለተኛው ዙር ያለፉት ሁለት ታውቀዋል፡፡  ፉክክሩም በመሃል ዘመሙ ኢማኑኤል ማክሮንና የቀኝ ፅንፈኛው የፓርቲ ማሪን ለ ፔን  መካከል እንደሚሆን ታውቋል ፡፡

በምርጫው ኢማኑኤል ማክሮን 23 ነጥብ 9በመቶ ድምፅ በማግኘት በቀዳሚነት ሲያሸንፉ ማሪን ለ ፔን  ደግሞ 21 ነጥብ 4 በመቶ ድምፅ በማግኘት በሁለተኛነት ፉክክሩን ማሸነፍ ችለዋል፡፡

በፖለቲካው መድረክ አዲስ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የ39 ዓመቱ ሚስተር ማክሮን ፈረንሳይን በፕሬዚዳንትነት በመምራት አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ሆላንዴ የኢኮኖሚ ሚኒስትር የነበሩት ሚስተር ማክሮን‹‹ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ፕሬዚዳንታችሁ እሆናለሁ›› በማለት ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ 

የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰሩ የጠቆሙት ሚስተር ማክሮን  የሥራ ዕድል ፈጠራም ሌላው ትኩረት የሚሰጡት ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከአገሪቱ የእንደራሴ ምክር ቤት መቀመጫዎች ግማሽ ያህሉ በሴቶች እንዲያዙ እፈልጋለው ብለዋል ፡፡

ሚስተር ማክሮንን በመከተል ወደ ቀጣዩ ምርጫ ያለፉት የቀኝ ፅንፈኛው ፓርቲ መሪ ማሪን ለ ፔን  ፈረንሳይን ከአውሮፓ ህብረት የማውጣት ሃሳብን በማቀንቀን ይታወቃሉ፡፡ ስደትን መቀነስ፣ነፃ የንግድ እንቅስቃሴን መግታትም የእጩዋ ፍላጎት እንደሆነ በይፋ ተገልጿል ፡፡

ለ ፔን  ድምፅ የሰጣቸውን ህዝብ በማመስገን ፈረንሳይን ወደ ፊት ለማራመድ የተደረገ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡ በመጀመሪያ ዙር ድምፅ ያልሰጣቸው ህዝብ በቀጣዩ ምርጫ ድምፁን በመስጠት በእሳቸው መሪነት የተሻለች ፈረንሳይ እንዲመለከት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረትን የማጠናከር ፍላጎት ያላቸው ሚስተር ማክሮን  ከጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ማርኬል እና ከአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ጄን ክላውድ የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክት ደርሷቸዋል፡፡

ወጣቱ ሚስተር ማክሮን ግንቦት ሰባት ቀን 2017 በሚካሄደው ምርጫ ለአሸናፊነት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር ፉክክር አምስተኛ ሆነው ያጠናቀቁት የሶሻሊስት ፓርቲ ዕጩ ቤኖይት ሃሞን ደጋፊዎቻቸው ለሚስተር ማሮን ድምፅ እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡

በ60 ዓመታት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዋነኞቹ የቀኝ ክንፍና የግራ ክንፍ ፓርቲ ተፎካካሪዎች ወደ ሁለተኛው ዙር ያላለፉበት ምርጫ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡