የአሜሪካ ግዙፍ ባህር ሰርጓጅ መርከብ ደቡብ ኮሪያ ደርሳለች

 

በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለው ውጥረት መጨመሩን ተከትሎ አሜሪካ ባህር ሰርጓጅ የጦር መርከቧን ወደ ደቡብ ኮሪያ አስገብታለች፡፡

ሰሜን ኮሪያ የወታደራዊ ምስረታ በዓሏን ለማክበር ዝግጅት ላይ ሆና ሚሳኤል ለማስወንጨፍ እየዛተች መሆኑን ተከትሎ ውጥረቱ ተባብሷል፡፡

ዋሽንግተንም ይህን የፒዮንግያንግ ተንኳሽነት ለመመከት ጦሯን ወደ ቀጣናው እያስገባች ነው፡፡

በደቡብ ኮሪያ ባህር ዛሬ የደረሰችው የአሜሪካ የባህር ኃይል የጦር መርከብ ሚሳኤል ተሸካሚዋ ዩ ኤስ ኤስ ሚቺጋን ናት፡፡

ዩ ኤስ ኤስ ሚቺጋን ባህር ሰርጓጅ መርከብ ሚሳኤል አስወንጫፊ ስትሆን፥ የጦር አውሮፕላንኖችን ከምትሸከመዋ ካርል ቪንሰን ጋር ተጣምራ ልምምድ ታደርጋለች ተብሏል፡፡

ሰሜን ኮሪያ 85ኛ ዓመት የወታደራዊ የምስረታ በዓሏን ዛሬ የምታከብር ሲሆን፥ በዚህ ሁነት ላይም ፒዮንግያንግ ሚሳኤሎችን ልታስወነጭፍ እንደምትችል ተጠቁሟል፡፡

በዋሽንግተን እና ፒዮንግያንግ መካከል የቃላት ጦርነትና ወታደራዊ ዛቻዎች የታጀበው የልሳነ ምድሩ ውጥረት፥ የአሜሪካን ብሔራዊ ምክር ቤት ባልተለመደ ሁኔታ ነገ በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ እንዲመክር አስገድዶታል፡፡

ዋሽንግተን ወደ ደቡብ ኮሪያ የላከቻት ዩ ኤስ ኤስ ሚቺጋን ባህር ሰርጓጅ መርከብ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ታጥቃለች።

ከዚህ ባለፈም 154 ቶምሃውክ ክሩዝ ሚሳኤሎችን መሸከሟ ነው የተነገረው።

በተጨማሪም 60 የልዩ ግዳጅ ወታደሮችን እና አነስተኛ ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ይዛለች፡፡

ፒዮንግያንግ በበኩሏ የአሜሪካን አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ እንደምታሰጥም ዝታለች፡፡

እንዲሁም በማንኛውም ጊዜ በአሜሪካ የባህር ሃይል ላይ ጥቃት እንደምትሰነዝርም ነው ያስጠነቀቀችው፡፡