በፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሩስያ ድጋፍ ባላቸው የመረጃ መረብ ጠላፊዎች ሰለባ መሆኑ ተገለጸ ።
ሩሲያ በበኩሏ ከደሙ ንፁህ መሆኗን በመጠቆም ውንጀላውን አጣጥለዋለች፡፡ ፈረንሳያውያን ለወጣቱ ዕጩ ተፎካካሪ ኢማኑኤል ማክሮን ድምፃቸውን እንዲሰጡ ግፊቱ አይሏል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው ለማሸነፋቸው የሩስያ ስውር እጅ እንዳለበት ሲናፈስ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሩስያ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ የነበሩት ሂላሪ ክሊንተን በምርጫው እንዲያሸንፉ ፍላጎት ስላልነበራት ነው የተባለው፡፡
ይህን የሚያረጋግጥ ማስረጃዎችን ማግኘቱንም የአሜሪካ የምርመራ ቢሮ አስታውቋል፡፡
ዛሬም በፈረንሳይ ተመሳሳይ ሀሜት እየተሰማ ነው፡፡ 11 ዕጩዎችን አፋጦ የመጨረሻዎቹን ሁለት ተፎካካሪዎች ለቀጣይ ዙር ያበቃው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሁንም አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ምርጫው በሩስያ እንደሚደገፉ በሚጠረጠሩ የመረጃ መረብ ጠላፊዎች ሰለባ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
በዚህ የህገ ወጥ ድርጊት ዋና ተዋናይነት ሩስያ እየተወነጀለች ነው፡፡ በመጀመሪያው ዙር የፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በቀዳሚነት ያጠናቀቁት ለዘብተኛው ኢማኑኤል ማክሮን እንዲያሸንፉ የማትፈልገው ሩስያ ብርቱ ትግል እያደረገች ነው ተብሏል፡፡
ማክሮን በምርጫው እንዳያሸንፉ በመረጃ መረብ ጠላፊዎች ዘመቻ መከፈቱን ያስታወቀው ተቀማጭነቱን በቶክዮ ያደረገው ትሬንድ ማክሮ የተሰኘ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡
ሩስያ ማክሮንን በመከተል ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፉት የቀኝ ፅንፈኛው ፓርቲ ማሪን ለ ፔን እንዲያሸንፉ ፍላጎት ስላላት በስውር ዘመቻውን እየደገፈች መሆኑ ነው ሲኤን ኤን የዘገበው፡፡
የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው በምርጫው ውስጥ ጣልቃ በመግባት አገራቸው ምንም የምታተርፈው ነገር እንደሌለ ጠቁመው ውንጀላውን አጣጥለዋል፡፡ የሚናፈሰው ወሬም መሰረተቢስ ነው ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው የቀኝ ፅንፈኛው ፓርቲ መሪ ለ ፔን ከሩስያ ጋር ጥሩ ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው በማስታወስ ሩስያ ይህን ሃሳብ ስለምትፈልግ ሴትዮዋ እንዲያሸንፉ የበኩሏን ከማድረግ ወደ ኋላ አትልም ይላሉ፡፡
ሚስ ማርያ ለ ፔን በሩስያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በመቃወምም ይታወቃሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፈረንሳይ ሩስያ አባል ካልሆነችበት ከሰሜን ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባልት እንድትወጣም ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ተደማምረው ሴትዮዋ በሩስያ መደገፋቸው አያጠራጥርም ነው የተባለው፡፡
የፈረንሳይ ከፍተኛ ባለስልጣናት በበኩላቸው ይህን መሰሉን ህገ ወጥ ድርጊት በመከላከል ምርጫው ያለምንም ችግር እንዲከናወን የሚበቅባቸውን እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ የተሳሳተ መንገድ ላይ የሚጓዝ ካለም ከድርጊቱ ሊታቀብ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡ ጉዳዩንም በጥልቀት እንደሚመረመንሩት አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ ወጣቱ ማክሮን ቀጣዩ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ቅስቀሳው ተጠናክሯል፡፡ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ሆላንድን ጨምሮ የተለያዩ አካላት የፈረንሳይ ህዝብ ድምፁን ለማክሮን እንዲሰጡ እያሳቡ ነው፡፡
በመጀመሪያው ዙር ሶስተኛና አምስተኛ የወጡት ፍራንስዎ ፊሎንና ቤኖይት ሃሞን ደጋፊዎቻቸው ለሚስተር ማክሮን ድምፅ እንዲሰጡ አሳበዋል፡፡ ማክሮንን ለአሸናፊነት የማብቃት ዘመቻው ተጧጡፎ መቀጠሉን ነው ሲኤንኤንና ሮይተርስ በስፋት የዘገቡት፡፡