ቻይና ተዋጊ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብን ለመጀመሪያ ጊዜ በመሥራት ለዓለም አስተዋወቀች ።
ቻይና የሠራቺው አዲስ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከብን በቀጣናው ያላትን ወታደራዊ አቅም ለማጠናከሯል ትልቅ ማሳያ ነው ተብሏል ።
የዓለም ሁለተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ቻይና ወታደራዊ አቅሟን ማጠናከሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ ወታደራዊ አቅሟን ማሳደጓን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ ፡፡
ቻይና በታሪኳል የመጀመሪያ ነው የተባለውን የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ገንብታ ሰሞኑን ለዓለም ማስተዋወቅ ችላለች ፡፡
ቻይና በሶቭየት ህብረት ተሰርቶ ከ25 ዓመት በፊት ከዩክሬን የገዛችው ሊዮኒንግ የተባለ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ባለቤት ነች፡፡ በራሷ አቅም ተዋጊ የጦር አውሮፕላኖችን ተሸካሚ ግዙፍ መርከብ በአገር ውስጥ ስትሰራ ግን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
አዲሱ መርከብ ከቀደመውና 60ሺ ቶን የመሸከም አቅም ካለው መርከብ ተሻሽሎ የተገነባ መሆኑን ነው ቢቢሲ በዘገባው ያመለከተው፡፡ የመርከቡ ሥራ እኤአ በ2013 መጀመሩን የቻይና መንግስት የዜና ምንጭ ዠንዋ አስታውቋል፡፡
ቻይና ግንባታውን አጠናቃ ለዓለም ያስታዋወቀችው ስም ያልተሰጠው መርከብ አስፈላጊው ነገር ከተሟላና የባህር ላይ ሙከራ ከተደረገ በኋላ እኤአ በ2020 ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተነግሯል፡፡ መርከቡ የቻይና ሰሜን ምስራቅ ወደብ በሆነችው ዳሊያን ባህር ላይ እንዲንሳፈፍ ተደርጓል፡፡
መርከቡ ሼንያንግ ጄ 15 የሚባሉትን 24 የቻይና ተዋጊ የጦር አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮችን እንደሚሸከም የአገሪቱ መካለከያ ሚኒስቴር አሰታውቋል፡፡
የመርከቡ አጠቃላይ የመጫን አቅምም 50ሺ ቶን ነው ተብሏል፡፡
የመርከቡ ግንባታ መጠናቀቅ ይፋ ሲደረግ በተዘጋጀው ፕሮግራም የቻይና ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ፋን ቻንግሎን ጨምሮ የተለያዩ የቻይና መንግስት ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
የቻይና እርምጃ በቀጣናው ወታደራዊ አቅሟን የማጠናከሯ ማሳያ ነው ሲሉ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች አስተያያት እየሠጡበት ይገኛል ፡፡
በተለይም ሰሜን ኮርያን ያስቆጣው የአሜሪካ ባህር ኃይል በኮርያ ባህረ ሰላጤ ወታደራዊ አቅሙን እያጠናከረ መምጣቱን ተከትሎ ቻይና ይህን እርምጃ መውሰዷ በራሱ የሚያስተላልፈው መልዕክት እንዳለ እየተገለጸ ነው፡፡
ቻይና ከሁለት እስከ አራት የሚደርሱ ሌሎች ተጨማሪ ተዋጊ የጦር አውሮፕላኖችን መሸከም የሚችሉ ግዙፍ መርከቦችን የመስራት እቅድ እንዳላት ኤቢሲ ጠቁሟል፡፡ ህንድ፣ጃፓንና ታይዋን የቻይናን ድርጊት በስጋትነት እንደሚመለከቱት ዘገባው ጨምሮ ገልፃል፡፡ (ምንጭ: ቢቢሲ)