የቀድሞዋ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚደንት ተጨማሪ የስምንት ዓመት አሥራት ተበየነባቸው

የደቡብ ኮሪያው ፍርድ ቤት በቀድሞዋ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ላይ ተጨማሪ የስምንት ዓመት እስራት በየነ፡፡

ፍርድ ቤቱ ፓርክ ጉይን ሄይ ላይ እስራቱን ያስተላለፈው በ16 ወንጀሎች ጥፋተኛ መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ ነው፡፡

እኤአ ከ2013 እስከ 2017 ደቡብ ኮሪያን በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት የ66 ዓመቷ ፓርክ ጉይን ሄይ ሙስናን እና ጣልቃ ገብነትን ጨምሮ የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ከቀረቡለት 18 ክሶች መካከል 16ቱን ፈፅመዋል ሲል ቀድሞ ከበየነባቸው የ24 ዓመታት እስር ላይ ስምንት ዓመት ተጨማሪ የማረሚያ ቤት ቆይታ እንዲኖራቸው ወስኗል፡፡

የሴዑል ማዕከላዊ ፍርድ ቤት በፍርድ ወቅት ፓርክ ጉይን ሄይ በተለይ እኤአ በ2016 የፓርላማ ምርጫ ላይ ጣልቃ ገብተዋል፣ 26 ነጥብ 5 ቢልዮን ዶላር የመንግስት ገንዘብም አጥፍተዋል ሲል በይኗል፡፡

የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያሳየው ገንዘቡ ለሃገሪቱ የደህንነት ተቋም ለልዩ ልዩ ስራዎች እየተባለ በየዓመቱ የሚመደብ ሲሆን በድርጊቱ ላይ ከቀድሞዋ ፕሬዝዳንት በተጨማሪ የተቋሙ የቀድሞ ሶስት ዳይሬክተሮችም የእስራት  ተበይኖባቸዋል፡፡

ሁለቱ ዳይሬክተሮች እያንዳንዳቸው በሶስት ዓመት ከስድስት ወር እና አንዱ ደግሞ ሶስት ዓመት እንዲታሰሩ ተወስኖባቸዋል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት በደቡብ ኮሪያ ታሪክ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ አሸንፈው ሥልጣን ላይ የወጡት የቀድሞዋን የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ፓርክ ጉይን ሄይን በመቃወም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደቡብ ኮሪያውያን የሥልጣን ይልቀቁ እና ለፍርድ ይቅረቡ በማለታቸው የስልጣን ጊዜያቸው ሳያበቃ ከሥልጣን ተነስተዋል፡፡ 

ፍርድቤቱ ቀድሞ የሠጠው የ24 ዓመት እስራት በተጨማሪ ዓርብ ዕለት ያሳለፈውን የእስር ውሳኔ ተዳምሮ የ66 ዓመቷ ፓርክ ጉይን ሄይ የ32 ዓመት የእስርቤት ኑሮ ይጠበቅባቸዋል፡፡(ምንጭ: አልጀዚራና ሮይተርስ)