አሜሪካና ፓኪስታን በኢኮኖሚ ዘርፍ ሽብርተኝነት ለመዋጋት አብረው እንደሚሠሩ ተገለጸ

አሜሪካና ፓኪስታን በኢኮኖሚው ዘርፍና ሽብርተኝነትን በመዋጋት አብረው እንደሚሰሩ ተገለፀ፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዩ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ፓኪስታን ገብተዋል፡፡

በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተመርጠው ወደ ሥልጣን የመጡት የቀድሞው የአሜሪካ ስለላ ተቋም ኋላፊ ማይክ ፖምፒዩ ተዳክሟል እየተባለ ይተች የነበረውን የትራምፕ አስተዳደር የዲፕሎማሲ ፖሊሲ ውጤት እንዲያስመዘግብ እየታተሩ ይገኛሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሜሪካ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር አሁን ከአፍጋኒስታን ጋር ባለው አለመግባባት እና በአፍጋኒስታን ባለው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን  ታሊባን ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያስችላቸውን ውይይት ለማድረግ ፓኪስታን ገብተዋል፡፡

ማይክ ፖምፒዮ በፓኪስታን አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሀንን እና የሀገሪቱን ወታደራዊ ጦር አዛዥ ካማር ጃቫደ ባጃዋ አግኝተው የመከሩ ሲሆን ዋሽንግተን ድጋፍ የምታደርግላት ኢስላማባድ በድብቅ በአፍጋኒስታን ላለው የታሊባን ታጣቂ ቡድን እርዳታ ታደርጋለች በማለት ዋሽንግተን ብትወቅስም ፓኪስታን ግን መሠረተ ቢስ ስትል አስተባብላለች፡፡

ይህ ጉዳይ ከቅርብ አመታት ወዲህ አሜሪካና ፓኪስታንን እያራራቀ ቢመጣም ሁለቱ ሀገራት አሁንም አብረው እንደሚሰሩ እና በአፍጋን የሚገኘውን የታሊባን ታጣቂ ቡድን ለማበርከክ ማይክ ፖምፒዮ ኢስላማባድ መግባታቸው ማሳያ ነው፡፡

ማይክ ፖምፒዮ በፓኪስታኑ ጉብኝታቸው የአሜሪካን የባህር ኋይል አዛዥ ጀነራል ጆሴፍ ደንፎርድን አብር ይዘው የተጓዙ ሲሆን ሰውየው እንዳሉት የፕሬዝዳንት ትራምፕ የደቡብ እስያ እስትራቴጂ ለፓኪስታን መልካም ውጤት የሚያስገኝ እና በአፍጋኒስታን የሚገኘውን የታሊባን ታጣቂ ኃይል ወደ ሰላም ድርድር የሚያመጣ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

አሜሪካ በዚህ አመት በአፍጋኒስታን የሚገኘውን የታሊባን ታጣቂ ለማንበርከክ ካሰማራችው ወታደር ባለፍ ለፓኪስታን ስምንት መቶ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረገች ሲሆን አሜሪካ አሁንም ፓኪስታን ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ለምታደርገው ብድር ዋስ እንድትሆን እና ኢኮኖሚዋን እንድትደግፍ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሀን ከማይክ ፒምፒዮ ጋር መወያየታቸው ነው የተገለፀው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፒዮ ከፓኪስታን ጉብኝታቸው በኋላ ወደ ህንድ በማቅናት ሀገሪቱ ከኢራን የምትገዛውን ነዳጅ እንድታቆምና ከሩሲያ የምታስገባን የሚሳኤል ምርት እንድታቋርጥ በከፍተኛ ኋላፊዎች ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ ነው የተነገረው፡፡

ማይክ ፖምፒዮ ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ጅም ማቲስ ጋር በመሆን በኒውዴሊህ ቻይና በቀጠናው ላይ እያሳደገችው የመጣችውን ወታደራዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ከህንዱ አቻቸው ጋር እንደሚመክሩም ታውቋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ኢራን ለህንድ ከፍተኛዋ ነዳጅ አቅራቢ ሀገር ስትሆን ሁለት ሶስተኛው የወታደራዊ መሣሪዋ ደግሞ በቀጥታ ከሩሲያ የሚገባ ነው፡፡

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  አሁን ህንድ ከእነዚህ ሁለት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቆም የሚያስችላቸውን ድርድር ሐሳብ ይዘው ወደ ህንድ የሚጓዙ ቢመስሉም የሚሳካላቸው ግን አይመስልም፡፡

የህንድ መከላከያ ሚኒስትር ግን ሀገሪቱ አሁን ላይ ከቻይና የሚደርስባትን ተፅዕኖ ለመቀልበስ  ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ መሣሪያዎችን ለመግዛት ስምምነት ፈፅማ የጨረሰች እንደሆነች እና ኤስ 400 ሚሳኤሎችን እየገዛችም እንዳለች ነው የገለፁት፡፡

ከኢራን ጋር ቢሆንም ህንድ ሙሉ ለሙሉ የምታስገባውን የነዳጅ ምርት እንደማታቋርጥ እየገለፀች መገኘቷ የአሜሪካን ፍላጎት ፉርሽ ሊያደርገው ይችላል እየተባለ ነው፡፡