ሳውዲ አረቢያ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ መገደሉን አረጋገጠች

ሳዑዲ አረቢያ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ በቱርክ መዲና ኢስታንቡል ውስጥ በሚገኘው የቆንጽላ ጽህፈት ቤቷ ውስጥ መገደሉን አረጋገጠች ፡፡

ሳውዲ አረቢያ በጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ አሟሟት ዙሪያ እወነታነት ያለው መረጃ ለመስጠት ስትወዛገብ ቆይታለች፡፡ የሳውዲአረቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድለ አል ጁብሪ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ በቆንስላ ጽህፈት ቤት ውስጥ አልተገደለም እያለች ስትከራከር መቆየቷም ይታወሳል፡፡

ነገር ግን የቱርክና የሳዑዲ የምርመራ ቡድኖች ቆንስላውን መርምረው ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ሳውዲ አረቢያ የመጀመሪያውን አቋሟን በመቀየር ጀማል ካሾጌ ኢስታንቡል በሚገኘው የሳውዲ ቆንጽላ መሞቱን አስታውቃለች፡፡

ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ እንደፈረንጆቹ ጥቅምት ወር ላይ ወደ ሳውዲ ቆንፅላ ጽህፈት ቤት ሲገባ መታየቱን መሰረት በማድረግ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጀማል ካሾጌ መሞት ሳውዲ አረቢያ ኋላፊነቱን ትወስዳለች ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡

የቱርክ ባለስልጣናት ደግሞ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ በሳውዲ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ላይ የሰላ ትችት የሚያቀርብ በመሆኑ ሳውዲ ባለስልጣናት እንዳስገደሉት ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡

አሁን ከብዙ ውዝግብ በኋላ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ በሳውዲ አረቢያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት አካባቢ መገደሉን እና አሟሟቱም በፀብ ምክንያት እንደነበር አምናለች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አል ጁብሪ የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ አሟሟት ነፍስ ማጥፋት ተግባር ነው ያሉ ሲሆን አሁን ስለ አሟሟቱ ሁሉንም ተጨባጭ መረጃዎች ሰብስበው በወንጀሉ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎችን ለመቅጣት እንደሚሰሩ ነው የገለፁት፡፡

የጋዜጠኛውን መሞት ተከትሎ ሳውዲአረቢያ በወሰደችው እርምጃ የሀገሪቱን ምክትል ደህንነት አህመድ አልሳሪ እና ሳውድ አልካቲኒን ከስልጣን ያባረረች ሲሆን 18 ዜጎቿንም ወደ ዘብጥያ አውርዳለች፡፡

የሳውዲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አክለውም ጀማል ካሾጌ መገደሉን ሳውዲ ትመን እንጅ ነገር ግን አስክሬኑ የት እንደሚገኝ አንዳችም አመላካች ነገር አለመኖሩን ነው የገለፁት፡፡

ነገር ግን ይህ አስነዋሪ ተግባር በአልጋ ወራሹ ንጉስ ሙሀመድ ቢን ሳልማን እንዳልተቀነባበረ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

ከጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ መሞት በኋላ ሳውዲ ደህንነት መዋቅሯን በአዲስ ለማደራጀትም ወስናለች፡፡

ሳውዲአረቢያ የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌን መሞት ከማመኗ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የአለም ሀገራት የተለያዩ ሀሳቦችም እየተንፀባረቁ ነው፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከጋዜጠኛው አሟሟት ጋር ተያይዞ ሳውዲአረቢያ የማጭበርበር ስልት ብትጠቀምም እውነቱ ግን ተዳፍኖ አልቀረም ብለዋል፡፡ ይሁንና ትራምፕ ከጋዜጠኛ ካሾጌ ሞት ጋር ተያይዞ የንጉስ ሙሀመድ ቢን ሳልማን እጅ እንደሌለበት እና ግኑኝነታቸውም እንደሚቀጥል ነው የገለፁት፡፡

የፈረንሳይ ጀርመን እና የብሪታኒያ መንግስታት ባወጡት የጋራ መግለጫ ደግሞ በጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ መሞት እንዳዘኑ እና ይሄ ግድያ አምባገነንነት በመሆኑ በጥብቅ እንደሚያወግዙ ነው የገለፁት፡፡

ባህረ ሰላጤው ሀገራትም በተመሳሳይ የጋዜጠኛው አሟሟት እጅግ ህገ ወጥነት የተሞላበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያሉት ሲሆን የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲቭ ጣይብ ኤርዶሀን ደግሞ ማክሰኞ በሚኖራቸው የፓርላማ ውይይት ላይ የጋዜጠኛውን ድብቅ አሟሟት ይፋ አደርጋለሁ ነው ያሉት፡፡

ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጌ ኢስታንቡል ወደ ሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ የገባው ከ18 ቀናት በፊት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ (ምንጭ፤ቢቢሲ)