የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያ አቻቸው በፌሬንጆቹ አዲስ አመት ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚገናኙ ተገለጸ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በፈሬንጆቹ 2019 አዲስ አመት ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው እንደሚወያዩ ተገለጸ፡፡

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በኮሪያ ልሳነ ምድር በነበረው የኒዩክለር ጦር መሳሪያ ግንባታ የተነሳ ባላንጣነት ፈጥረው የቆዩ ቢሆንም እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር ባለፈው ሰኔ ወር በሲንጋፖር ውይይት በማድረግ ወደ ሰላም መመለሳቸው የሚታወስ ነው፡፡

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ኪም ጆንግ ኡን ለሁለተኛ ጊዜ በፈረንጆች አዲስ አመት ተገናኝተው እንደሚወያዩ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ሁለቱ መሪዎች ለሁለተገኛ ጊዜ ተገናኝተው ሲመክሩ ባለፈው  በሲንጋፖር ተገናኝተው የፈፀሟቸውን ስምምነቶችና የገቡት ቃል ግን እንደማይፈርስም አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ውይይታቸውም በተለይ የሰሜን ኮሪያ መስመር ያልያዘውን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ትጥቅ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጡትም ነው የተገለፀው፡፡

ም/ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ እንደገለጹት የሁለቱ መሪዎች ሁለተኛው ውይይት በአዲሱ አመት የመጀመሪያው ወር ላይ የሚካሄድ ቢሆንም መሪዎች የሚወያዩበት ከተማ ግን አልታወቀም፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንት ፔንስ ይህንን የተናገሩት ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙንጃኢን ጋር በሲንጋፖር የኢስያ ፓስፊክ ሀገራት የጋራ ስብሰባን ከተካፈሉ በኋላ ነው፡፡

የአሜሪካ የውስጥ ምንጮች እንደገለፁት አሁን ላይ በሰሜን ኮሪያ የድብቅ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ማበልፀጊያ ተቋማት እንደሚገኙ በመግለፅ በአሁኑ ስብሰባቸውም ኪም ጆንግ ኡን ይህንን ፕሮግራማቸውን እንደሚተውም ይጠበቃል፡፡

ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው ለማውራት ፍላጎት እንዳላቸው የገለፁት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ በተጣለባት ማእቀብ ዙሪያ እና በኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ላይ ሰሜን ኮሪያ የተባለችውን እንድትፈፅም መግባባት ላይ እንደርሳለን ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡

ም/ፕሬዝዳንት ፔንስም ሆነ የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙንጃኢንም የትራምፕ እና ኪም የሁለተገኛው ውይይት እንዲሳካ እንደሚሰሩ ፍላጎት እንዳላቸው ነው የገለፁት፡፡

ይህ ይሁን እንጅ ሀገሪቷ የተባለችውን እስክትፈፅም በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለው ማእቀብ ግን እንዲለዝብ አሜሪካ አልፈለገችም፡፡

የሰሜን ኮሪያ የንግድ አጋር እንደሆነች የሚነገርላት ቻይናም ማዕቀቡ እንዲቀጥል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ሺ ዥንፒንግ ጋር መወያታቸውን እና ቻይናም ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር ግንባታዋን እስክታቆም ማዕቀቡን እንደምትደግፍ ነው የገለፁት፡፡

ሰሜን ኮሪያም ላለፉት ወራቶች ሚሳኤል ሙከራዋን ብታቆምም ነገር ግን አሜሪካ ማዕቀቡ እንዲነሳ ካላስደረገች የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታዋን መልሳ እንደምትጀምር እያስጠነቀቀች ነው፡፡ (ምንጭ፡- ሮይተርስ)