የአዉሮፓ ህብረት በብራሰልስ ባደረገው ስብሰባ የብሪታንያን ከህብረቱ ልዉጣ ጥያቄ ተቀብሎ አጸደቀ

የአዉሮፓ ህብረት መሪዎች በቤልጄም ብራሰልስ ባደረጉት ስብሰባ የብሪታንያን ከህብረቱ ልዉጣ ጥያቄ ተቀብለዉ ማፅደቃቸዉ ተነገሯል።

ከ20 ሳምንታት ድርድር በኋላ የአዉሮፓ ህብረት አባል ሀገራት 27 መሪዎች በቤልጀም ብራሰልስ ተሰባስበዉ የብሪታንያን ከህብረቱ አስወጡኝ ጥያቄ ተቀብለዉ አፅድቀዋል።

አንድ ሰዓት ባልሞላ ዉይይት ዉስጥ ዉሳኔዉን ያስተላለፉት የአባል ሀገራቱ መሪዎች ብሪታንያ በቀጣይ ከህብረቱ ጋር ሊኖራት ስለሚችለዉ ግንኙነትና አጋርነት ዙሪያም መክረዋል።

በርግጥ የህብረቱ መሪዎች የብሪታንያን የመነጠል ጥያቄ ቢቀበሉትም ዉሳኔዉ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ትግበራ የሚገባዉ ግን የብሪታንያን ፓርላማ ይሁኝታ ሲያገኝ በመሆኑ የሀገሪቱ ፓርላማ በቀጣይ የሚያስተላልፈዉ ዉሳኔ ተጠባቂ ሆኗል።

የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ለብሪታንያዊያን ዜጎቻቸዉ ባስተላለፉት መልዕክት የአዉሮፓ ህብረት ያስተላለፈዉ ዉሳኔ ለብሪታንያ ቀጣይ እድገትና ብልፅግና እንደ ብስራት ዜና የሚቆጠር ነዉ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ሜይ አክለዉም ከእንግዲህ በብሬግዚት ጉዳይ በመከራከር ጊዜ የምንፈጅበት ወቅት ሳይሆን ተባብረን ለሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ ተባብረን መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ ተደምጠዋል።

ብሪታንያ ከህብረቱ እንድትወጣም ሆነ በህብረቱ እንድትለይ ድምፃቸዉን የሠጡ የሀገሪቱ ዜጎች ሁሉ አሁን ልዩነታቸዉን አርቀዉ ስለቀጣይ የሀገራቸዉ አዲስ መንገድ ማሰብ እንደሚገባቸዉም አስገንዝበዋል።

የብሪታንያ ከህብረቱ የመዉጣት ጉዳይ ከፈረንጆቹ መጋቢት 2017 ጀምሮ በክርክርና በዉዝግብ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ህብረቱ ያስተላለፈዉን ዉሳኔ ተከትሎ ግን ብሪታንያ በእኛ አቆጣጠር መጋቢት 22 ወይንም በፈረንጆቹ  በመጋቢት 29፣ 2019 ከህብረቱ የመዉጣቷ ነገር እዉን ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።

ሆኖም የዉሳኔዉን ቁርጥ ያለ ነገር ለማወቅ ግን የብሪታንያ ፓርላማ በእኛ አቆጣጠር ታህሳስ 5 ላይ የሚያስተላልፈዉ የመጨረሻ ዉሳኔ ይጠበቃል።

“እዉን የህብረቱ ዉሳኔ የብሪታንያን ፓርላማ ድጋፍ ያገኛል?” የሚለዉ ነገር ግን ስጋት ላይ ወድቋል።

በተለይም የሌበር፣ ሊብ ዴምስ፣ SNP፣ DUP እና ሌሎች በርካታ ወግ አጥባቂ ፓርላማ አባላት የብሪታንያን ከህብረቱ ልዉጣ ጥያቄ ዉድቅ ያደርጉታል ተብሎ ተሰግቷል።

ወግ አጥባቂዎቹ ድምፃቸዉን ይነፍጓቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም ጠ/ሚ ቴሬዛ ሜይ ግን ዜጎች ለዉሳኔዉ ድጋፋቸዉን ይቸሩ ዘንድ በመማጸን ላይ ናቸዉ ተብሏል።

ለዚህም ጠ/ሚ ሜይ ከህብረቱ መዉጣት ያለዉን በጎ ነገር በመዘርዘር ለህዝባቸዉ ለማስረዳት ጥረታቸዉን ቀጥለዋል።

በተለይም ዉሳኔዉ የመንቀሳቀስ ነፃነትን የሚያጎናፅፍ ስለመሆኑ፣ የዜጎችን ህገመንግስታዊ ታማኝነት የሚያሳድግ እንደሚሆንና ከዚህ ቀደም በሀገር ዉስጥ የወጡ ህጎች ብሪታንያ የህብረቱ አባል በመሆኗ ሳታስፈፅማቸዉ የቆዩትን ህጎችም በነፃነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላት በመሆኑ የህብረቱን ዉሳኔ መደገፍ ተገቢ ነዉ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ከዚያም ባለፈ ዉሳኔዉ ጂብራልታር የታላቋ ብሪታንያ ሆና እንድትቀጥል የሚያስችል በመሆኑ በዚህ ረገድም ስጋት እንዳይገባችሁ ሲሉ አክለዋል ጠ/ሚሯ።

በትላንቱ ዉሳኔ የአዉሮፓ ህብረት በሁለት ወሳኝ የብሬግዚት ሰነዶች ላይ ዉሳኔ አስተላልፏል።

የመጀመሪያዉ የህብረቱን የመገንጠል ስምምነት ሲሆን ብሪታንያ ከህብረቱ የወጣችበትን አካሄድ ያትታል።

ከዚያም ባለፈ ሀገሪቱ ከህብረቱ በመዉጣቷ ምክኒያት ስለምትከፍለዉ 39ቢሊየን ፓወንድም እንዲሁ።

በተጨማሪም ስለዜጎች መብትና በታላቋ ብሪታንያ ስር ያሉ ራስ ገዝ ግዛቶች ቀጣይ እጣ ፈንታም ጭምር የያዘ መዝገብ እንደሆነ ተነግሯል።

ሁለተኛዉ ሰነድ ደግሞ ብሪታንያና ህብረቱ ቀጣይ ሊኖራቸዉ ስለሚገባ ግንኙነት የሚያብራራ ሰነድ ነው ተብሏል፡፡

የአዉሮፓ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጂን ክላዉድ ጀንከር ስለ ትላንቱ ዉሳኔ ሲናገሩ በብሪታንያ ከህብረቱ መዉጣት ተደስቶ በደስታ የሻምፓኝ ብርጭቆዉን ያጋጨ አልነበረም፡፡

ይህም አባል ሀገራቱ የወሰኑት ዉሳኔ የዉዴታ ግዴታ እንደነበር የሚያሳይ ነዉ ብለዉታል።

ሆኖም አሁን ላይ ያለዉ የተሻለና ብቸኛ አማራጭ ግን ይሄ ብቻ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በርካቶቹ የህብረቱ አባል ሀራትም በዉሳኔዉ ደስተኛ ያልነበሩ ቢሆንም ሁሉም ግን የብሪታንያን ጥያቄ ተቀብለዉ አፅድቀዉታል።

ከብሪታንያ ጋር ያላቸዉ የወደፊት ግንኙነትም በተቻለ መጠን በመልካም ወዳጅነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ጠይቀዋል።

የብሪታንያን ከህበረቱ የመዉጣት ሂደት ሊያደናቅፉ የሚችሉ ስጋቶች አሁንም ቢሆን መኖራቸዉን መዘንጋት እንደማይገባ የቢቢሲዋ የፖለቲካ ጉዳዮች አርታኢ ላዉራ ኩንስበርግ ትገልፃለች።

በተለይም ዉሳኔዉ የፓርላማዉን ድጋፍ የማያገኝ ከሆነ ፓርላማዉ ያለ አንዳች ስምምነት ተበትኖ ሌላ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ በጉዳዩ ላይ ሊካሄድ እንደሚችል በመጠቆም።

ከዚያም ባለፈ የአዉሮፓ ህብረት ፓርላማ ቀጣይ ዉሳኔም ምን ሊሆን እንደሚችል አለመታወቁ የብሬግዚት ነገር ዛሬ ላይም እንዳልለየለት የሚያሳይ ነዉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።