የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ ጋር በተያያዘ ሲአይኤ ለአሜሪካ ሴናተሮች ማብራሪያ ሊሰጥ ነው ተባለ

የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ ጋር በተያያዘ ሲአይኤ ለአሜሪካ ሴናተሮች ማብራሪያ ሊሰጥ ስለመሆኑ ተገለጸ፡፡

የአሜሪካ ብዙኃን መገናኛዎች ምንጩን ሳይጠቅሱ ባወጡት ዘገባ መሰረት የሲ አይ ኤዋ ዳይሬክተር ጊና ሃስፐል በሳዉዲዉ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ሞት ዙሪያ ለተለያዩ የአሜሪካ ሴኔት ኮሚቴ ኃላፊዎች በዝግ በሚካሄድ ስብሰባ ማብራሪያ ሊሰጡ መሆኑ ተነግሯል።

ዘ ዎልስትሪት ጆርናል ባወጣዉ ዘገባ መሰረትም ማብራሪያዉ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

ሮይተርስ የዜና ምንጭ ለስብሰባዉ ቅርበት ያላቸዉን ሰዎች አነጋግሮ ባወጣዉ ዘገባ እንዳመለከተውም የሲአይኤዋ ዳይሬክተር ለአሜሪካ ሴኔት የዉጭ ጉዳይና ወታደራዊ ጉዳይ ሃላፊዎች ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ተጠብቋል።

የሴኔቱ የስለላ ኮሚቴ ቀድሞ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንደሰጠዉም መረጃዉ አመላክቷል። 

ከተባሉት የሴኔት ኮሚቴ አባላት ዉጭም ሌሎች የሴኔት አባላትም እንደሚሳተፉ ቢጠበቅም ሲአይኤ ግን ስለጉዳዩ ምንም የሰጠዉ ማረጋገጫ አለመኖሩ ነዉ የተነገረዉ።

ሲአይኤ ለጋዜጠኛዉ ግድያ የሳዉዲዉ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢንሰልማን ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሰጥተዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም የሳዑዲ መንግስት ግን በጋዜጠኛ ካሾጊ ሞት ልዑል አልጋ ወራሹ ምንም የሚያዉቁት ነገር እንደሌለ በተደጋጋሚ ሲያስተባብል ቆይቷል።

ባለፈዉ ሳምንት የአሜሪካ ከፍተኛ ባስልጣናት በጉዳዩ ላይ የመከሩ ሲሆን በወቅቱም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፒዮ ሀገራቸዉ እስካሁን ልዑል አልጋ ወራሹ የጋዜጠኛዉን ግድያ ስለማዘዛቸዉ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ ባለመኖሩ የአሜሪካ ሴናተሮች ከሳዉዲ ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማጣጣል ባይጣደፉ በማለት ነገሩን ለማብረድ ሞክረዋል ተብሏል።

ስብሰባዉን ተከትሎም አሜሪካ ሳዑዲን በመደገፍ በየመን እያካሄደች ያለዉን የጦር ዘመቻ እንድታቆምም ሴኔቱ በአብላጫ ድምፅ መወሰኑ ነው የተሰማው።

የ59 አመት የእድሜ ባለጸጋው ሟቹ የዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ አምደኛ የነበረዉ ጀማል ካሾጊ የሳዑዲዉን ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሰልማንን በሰላ ብዕሩ ክፉኛ ሲተች እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ባለፈዉ የፈረንጆቹ ጥቅምት 2 ላይ በቱርክ በሚገኘዉ የሳዑዲ ኢምባሲ ዉስጥ ተገድሎ መገኘቱ ይታወሳል፡፡ (ምንጭ፡- አልጀዚራ)