የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክርቤት በየመን ጦርነት ላይ ለሳውዲ የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም ወሰነ

የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አሜሪካ በየመን ጦርነት ለሳዉዲ የምታደርገዉን ድጋፍ እንድታቆም ዉሳኔ አስተላለፈ። ውሳኔዉ የፕሬዝደንት ትራምፕን አቋም የሚቃረን ስለመሆኑ ተነግሯል።

ከዛም በተጨማሪ ምክር ቤቱ የሳውዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ለጋዜጠኛና ፀሃፊ ጀማል ካሾጊ ሞት ተጠያቂ መሆን እንደሚገባቸውም ከውሳኔ ላይ ደርሷል።

የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ትላንት ሀሙስ ባካሄደዉ ስብሰባ በሳዑዲ ፊት አዉራሪነት በሚመራዉ የየመን ጦርነት አሜሪካ የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም የቀረበውን የውሳኔ ሓሳብ ተቀብሎ አፅድቋል።

ይህም የሀገሪቱ ኮንግረስና ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቀጣዩ አመት አሜሪካ ለሳዑዲ የምታደርገዉን ወታደራዊ ድጋፍ ታቁም ወይስ ትቀጥል በሚለዉ ጉዳይ ላይ የሚያደርጉትን ክርክር ተጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ምክር ቤቱ ባለፈዉ መስከረም ወር ላይ በቱርክ በሚገኘዉ የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ ለተገደለዉ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ጉዳይ የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ተጠያቂ መሆን እንደሚገባቸውም ዉሳኔ አስተላፏል።

ያኔ አልጄሪያዊዉ ሰው ሞሀመድ ቦአዚዝ በአደባባይ እራሱን በእሳት ሲለኩስ የጀመረዉ የአረቡ አለም አብዮት፣ በርካቶቹን የመካከለኛዉ ምስራቅ ሀገራት ለኩሶ ጠባሳ ያላሳረፈበት የአረብ ሀገር የለም።

አብዮቱ በርካቶቹን አምባገነን የአረብ መሪዎች ከስልጣን አሽቀንጥሮ ሲጥል እንደነ ሆስኒ ሙባረክና ሙአመር ጋዳፊን ደግሞ ለሞት ዳርጓል።

 

በፈረንጆቹ 2011 የአረቡ አለም በአብዮት ማዕበል ሲመታ የጀመረዉ የየመን ጦርነትም ባለፉት 7 አመታት ቆይታዉ በሀገሪቱ ያስከተለዉ ሞትና ዉድመት ከቃላትም በላይ ነዉ።

ፕሬዝደንት አሊ አብደላ ሳሌህን ከስልጣን ለመፈንገል ያለመዉ አብዮት አቅጣጫዉን ስቶና እንደነ ሳዑዲና ኢራን የመሰሉ በፅንፍ የቆሙ ተዋንያንም ገብተዉበት የሀገሪቱ ጦርነት የክፋት ጥግ ላይ ደርሷል።

ለጦርነቱ መክፋትና እዚህ መድረስ ደግሞ በጦርነቱ ያሉ ተዋንያን ማለትም ሳዉዲና ኢራን ድርሻ እጅጉን የጎላ ስለመሆኑ ይነገራል። አሜሪካና ሩስያም ቢሆን በእጅ አዙር በሚያደርጓቸዉ ደባዎች ለጦርነቱ መባባስ ከፍተኛ ባለድርሻዎች ናቸዉ።

በተለይም አሜሪካ ሳዑዲ አረቢያ በዚያ በየመን ምድር በንፁሃኖች ላይ የምታዘንባቸዉን ቦንቦች በማቅረብ የከፋ የጦር መዓት በሀገረ የመን እንዲደርስ ያደረገች ዋነኛዋ ሴረኛ ሆና ዛሬም ድረስ ዘልቃለች። በዚህ ሁሉ የፖለቲካ ቁማርተኞች የጦር ልፊያና ፍትጊያ ግን ዋነኞቹ ገፈት ቀማሾች ንፁሀኑ የመናዊያን መሆናቸዉ መላዉን አለም ያሳዘነ ሆኗል።

በርግጥ አሜሪካዊያን ዜጎችም ቢሆኑ ሀገራቸዉ ዘላለሟን በሀገራት የዉስጥ ጉዳይ ገብታ መፈትፈቷ በተለይም ደግሞ የየመኑ ጦርነት እዚህ እንዲደርስ ዋነኛዋ ተዋናይ ሃያሏ ሀገር መሆኗን ሲያስቡት ፖለቲከኞቻቸውን ይረግማሉ።

ሰሞንኑን አዲስ ነገር ግን ከሀገሪቱ ዜጎች በተጨማሪ የሀገሪቱ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትም ሀገራቸዉ ለአመታት በየመን ጦርነት ረዝሞ የቆየዉ እጇ ያጥር ዘንድ ከስምምነት ላይ መድረሳቸዉ ነው። በተለይም ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ የምክር ቤቱ አባላት የአሜሪካን የእጅ አዙር የየመን ተሳትፎ ክፉኛ ሲቃወሙና ሲተቹ እንደቆዩ ነዉ የተነገረዉ።

በትላንትናዉ የምክር ቤቱ ዉሳኔም 56ቱ የምክር ቤት አባላት ውሳኔዉን የደገፉ ሲሆን 41ዱ በአንፃሩ ዉሳኔዉን በመቃወም ድምፅ ሰጥተዋል። ዉሳኔዉን ከደገፉት 56 አባላት ዉስጥም 7ቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ ሰዎች ስለመሆናቸዉ ተነግሯል።

አሜሪካ በየመን ጦርነት የምታካሂደዉ ወታደራዊ ተሳትፎ በኮንግረሱ እዉቅና የሌለዉ እንደሆነም ነዉ መረጃዎች የሚያሳዩት። ይህም ሆኖ ዛሬም ድረስ የትራምፕ ሰዎች ኮንግረሱ የመከላከያ ተቋሙ ፔንታጎን ለሳዉዲ የሚያደርገዉን ወታደራዊ ድጋፍ እንዳያስቆም ተማፅኗቸዉን አበርትተዋል ተብሏል። 

የአሜሪካዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዎና የመከላከያ ሚኒስትሩ ጂም ማቲስ ለኮንግረሱ አባላት ባደረጉት ገለፃ አሜሪካ በየመን ያላትን ተሳትፎ ማስቀጠሏ የኢራንን የቀጠናዉ አካሄድ ከመግታት አንፃር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረዉ አብራርተዋል።

ሆኖም አብዛኞቹ የምክር ቤቱ አባላት ሳዑዲ በየመን የምታደርገዉን የጦርነት ዘመቻ አቁማ የየመን ጉዳይ በድርድር እንዲፈታ ይሻሉ።

ሁለቱ የየመን ተፋላሚ ኃይሎችም በዚህ ሳምንት በስዊድን ሪምቦ ባደረጉት ዉይይት በወደብ ከተማዋ ሆዴይዳ የሚያካሂዱትን ጦርነት ለማቆምና 16 ሺህ እስረኞችንም ለመለዋወጥ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሏል። ከዛም በተጨማሪ የሀዉቲ አማፂያን በቁጥጥራቸዉ ስር ያሉትን የየመን ወደቦች ለሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ነፃ ለማድረግ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሏል።

የአሁኑ የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ያስተላፈዉ ዉሳኔ ከ45 አመታት በፊት የወጣዉን የጦር አዋጅ ህግ ዳግም ተግባራዊ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላልም ተብሏል።

 ከ45 አመታት በፊት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን ተከታታይ የጦር ዘመቻዎችን በቬትናም ላይ መክፈታቸዉን ተከትሎ የሀገሪቱ ምክር ቤት የፕሬዝደንቱን ድርጊት የሚያስቆም ህግ በፈረንጆቹ 1973 ነበር የፀደቀው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮም የጦር ዘመቻ ማወጅ የሚያስችለው ከፍተኛ ሥልጣን ለኮንግረሱ እንደተቸረዉ ይነገራል።

በሳዑዲ አረቢያ የሚመራዉና እነየተባሩት አረብ ኢምሬቶች ያሉበት የጦር ጥምረት በፈረንጆቹ 2015 በየመኑ ጦርነት ጣልቃ ከገቡ ወዲህ የሀገሪቱን መንግስት በመደገፍ በሀዉቲ አማፂያን ላይ ከፍተኛ ዘመቻ መክፈቱም ነዉ የሚነገረዉ።

በዚህም ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ 85 ሺህ ህፃናት ብቻ በረሃብ ማለቃቸዉ ነዉ የሚነገረዉ። በርካቶቹ የሀገሪቱ ዜጎች በጦርነቱ፣ ረሃብና በኮሌራ በሽታ ለሞት የተዳረጉ ሲሆን አስፈላጊዉ ሰብዓዊ ድጋፍ በአፋጣኝ መዳረስ አለመቻሉ ደግሞ የየመናዊያኑን ስቃይ ከድጡ ወደማጡ አድርጎታል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።