የኮሪያን ልሳነ-ምድር ከኒውክሌር ለማጽዳት የተጀመረው ስራ ቻይና እንደምትደግፍ አስታወቀች

የኮሪያን ልሳነ-ምድር ከኒውክሌር ለማጽዳት የተጀመረው ስራ አበረታች ውጤት እንዲያስመዘግብ ቻይና የበኩሏን ድርሻ እንደምትወጣ የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሉ ካንግ ገልጸዋል፡፡

በኮሪያ ልሳነ-ምድር ሲጋጋል ዛሬ ላይ የደረሰው የፖለቲካ ሽኩቻ አሁን ላይ መለሳለስን አሳይቷል፡፡

ቀጠናውን ከኒውክሌር ነጻ ለማድረግም በሰሜን ኮሪያ በደቡብ ኮሪያና በአሜሪካ መካከል አበረታች ስራዎች ተጀምረዋል፡፡

አሜሪካና ሰሜን ኮሪያ የኮሪያን ልሳነ-ምድር ከኒውክሌር ለማጽዳት የደረሱትን ስምምነት ተፈፃሚ ለማድረግ የሚያግዝ ግብረ ኃይልም ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ አይዘነጋም፡፡

የኮሪያን ልሳነ-ምድር ከኒውክሌር ለማጽዳትና ቀጠናውን ሰላማዊ ለማድረግ የተጀመረው ስራ አበረታች ውጤት እንደሚያስመዘግብ ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሉ ካንግ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድም ቻይና የበኩሏን ድርሻ እንደምትወጣም ነው ቃል አቀባዩ የገለፁት፡፡

የኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን አዲሱን የፈረንጆች አመት አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት የኮሪያን ልሳነ ምድር ከኒውክሌር ለማጽዳት የተደረሰውን ስምምነት ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ አዎንታዊ ምልክቶችን ማሳየታቸው ይታወሳል፡፡

የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሉ ካንግ እንደተናገሩት ሰሜን ኮሪያ የኮሪያን ልሳነ ምድር ከኒውክሌር ለማጽዳት እየወሰደች ያለውን እርምጃ ቻይና ታደንቃለች፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰሜን ኮሪያ ፤ ደቡብ ኮሪያና ፤ አሜሪካ ለሚያደርጉት ግንኙነት ሀገራቸው ድጋፍ እንዳላት አስታውቀዋል፡፡

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት የኮሪያን ልሳነ ምድር ከኒውክሌር ለማጽዳት አስፈላጊና አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ  ይህን ጅማሪ ከግብ ለማድረስ የሚያስችሉ ንግግሮችና ድርድሮች መስመር መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

ቃል አቀባዩ አክለውም የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ አሜሪካና ሰሜን ኮሪያ የጀመሩትን ድርድር ሀገራቸው የምትደግፈው መሆኑንና  የተጀመረው ድርድርም አበረታች ውጤት እንዲያስመዘግብ ቻይና ድጋፏን እንደምታደርግ መግለጻቸውን አስታውቀዋል፡፡

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙን ጃይ ኢን በሴኡል ጉብኝት ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት ሚያሳይ ደብዳቤ መላካቸውም እንደ አበረታች ጅማሮ ሊወሰድ ይችላል፡፡/ሲጂቲኤን/