የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላን ወታደሮች እና ቁሳቁስ ጭኖ ካራካስ መግባቱ ተዘገበ

የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላን ለቬኒዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒሎላስ ማዱሮ ድጋፍ ወታደሮች እና ቁሳቁስ ጭኖ ካራካስ መግባቱ ተዘግቧል፡፡

እንደ ሩሲያው ስፑትኒክ የዜና ወኪል ባሳለፍነው ቅዳሜ ሁለት የሩሲያ ወታደረዊ አውሮፕላኖች ቁሳዊና ወታደራዊ ድጋፍ ለኒኮላስ ማዱሮ መንግስት ለማድረግ ካራካስ መድረሳቸውን አስነብቧል፡፡

የዜና ወኪሉ ዝርዝር መረጃ ባያስነብብም በመዲናዋ ካራካስ ከሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በረራው ምንም ሚስጥራዊነት እንደሌለው እና ቀደም ሲል በሀገራቱ መካከል በጉዳዩ ላይ የጋራ መግባባት እንዳለ ለመጠቆም ሞክሯል፡፡

የስፑትኒክ ዜና ወኪልን መረጃ ተከትሎ ጃቭዬር ማዮርካ የተባለ የቬኒዙዌላ ጋዜጠኛ ንብረትነታቸው የሩሲያ አየር  መንገድ የሆኑ አንቶኖቭ 124 ካርጎ ጫኝ እና አንድ መለስተኛ ጄት በካራካስ አየር ማረፊያ ቅዳሜ ዕለት ስለመታየታቸው በቲውተር ገፁ አስፍሮታል፡፡

በጄኔራል ቫሲሊ የሚመራ  100 ወታደሮችና 35 ቶን የሚገመት ቁሳቁስ በስፍራው መድረሱን ዘግይቶም ቢሆን የቬኒዙዌላው ሳንቲያጎ ታይምስ አስነብቧል፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገጾች የአውሮፕላኖቹን ፎቶ እማኝ ያደረጉ መረጃዎች በስፋት ወጥተዋል፡፡

የሩሲያን ሰንደቅ አላማ ያነገበ አውሮፕላን መታየቱንም ብዙዎች ተቀባብለውታል፡፡ የ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ጋዜጠኛ በቬኒዙዌላ ብሄራዊ ጥበቃ የታጀበ አውሮፕላን በአየር ማረፊያው ማየቱን አስነብቧል፡፡

በሌላ በኩል የቬኒዙዌላ ባለስልጣናት ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸውና ካራካስ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በወጡት ዘገባዎች ዙሪያ ምንም ለማለት እንዳልፈቀደ ታውቋል፡፡

ቬኒዙዌላ በፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ እና ተቀናቀኛቸው ጃይን ጉዋይዶ መካከል በከረረው ፍጥጫ የጎዳና ላይ ነውጥ እያስተናገደች ትገኛለች፡፡

ኣሜሪካ እና በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ከተቀናቃኙ ጃይን ጉዋይዶ ጎራ ሲሰለፉ ቻይና እና ሩሲያ  ደግሞ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን አይዞህ ባይ ናቸው፡፡ /ሲጂቲኤን/