ኮሜዲያን ዘለንስኪ በዩክሬን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸነፈ

ዩክሬናዊው ኮሜዲያን ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በሀገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በሰፊ ልዩነት አሸንፏል።

ለሀገሪቱ ፖለቲካ አዲስ የሆነዉ ኮሜዲያኑ ዘለንስኪ በምርጫው ከ70 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት እንዳሸነፈ ነው የተገለጸው፡፡

የ41 ዓመቱ ዘለንስኪ ከወቅቱ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ ጋር ተፎካክረዋል።

ፖሮሼንኮ በምርጫው መሸነፋቸውን ያመኑ ሲሆን፤ "አዲሱ ልምድ የሌላቸው የዩክሬን ፕሬዚዳንት በሩሲያ ጫና ውስጥ ይወድቃሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ አዲሱ የዩክሬን አመራር በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጉዳዮች ላይ የመራጮቹን ተስፋ እውን ለማድረግ መስራት እንዳለበት ገልጿል።

አዲሱ የምርጫ አሸናፊ ዘለንስኪ ደግሞ በቀጣይ ከተገንጣይ ወገኖች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

የዩክሬን ግዛት የነበረችው ክሬሚያ በፈረንጆቹ 2014 ወደ ሩሲያ መገንጠሏ የሚታወስ ሲሆን ከክሬሚያ መገንጠል በኋላ የዩክሬን ወታደራዊ ሃይሎች እና በሩሲያ የሚደገፉ ተገንጣይ ሃይሎች ውጊያ ላይ ናቸው የተባው።

(ምንጭ፦ቢቢሲ)