ኪም ጆንግ ኡን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሩሲያ ገቡ

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሩሲያ ገብተዋል፡፡

በጉብኝታቸው ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከፒዮንግያንግ በመነሳት በርካታ ጠረፎችን በማቋረጥ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ለሚኖራቸው ውይይት በባቡር ተጉዘው ሩሲያ ካሀሳን ድንበር ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

የሰሜን ኮሪያ የዜና ወኪል ኬሲኤንኤ እንደዘገበው ኪም ጆንግ ኡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ሪ ንግ ሆ እና የኒዩክሌር ተደራዳሪያቸውን ኮ ሶን ሁይን አስከተለው ነው ሩሲያ የገቡት፡፡

በባቡር መጓዝ የምንጊዜም ምርጫቸው እንደሆነ የሚነገርላቸው ኪም ጆንግ ኡን ግን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የምንጊዜም አጋራቸው እና በኒዩክሌር መርሀ ግብራቸው ደጋፊያቸው እንደሆኑ በማሰብ ነው ወደ ሩሲያ ያቀኑት፡፡

ኪም ጆንግ ኡን በሩሲያ በመጀመሪያቸው ይፋዊ ጉብኝታቸው በዋናነት ከፕሬዝዳንት ፑቲን ድጋፍ እንዲደረግላቸው አላማ ያደረጉ ሲሆን ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ  ዙሪያ  በሰፊው እንደሚመክሩም ይጠበቃል፡፡

ከአሜሪካ እና ምዕራባዊያን ሀገራት በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለመቀልበስ ኪም ጆንግ ኡን ከቻይናና ሩሲያ ጋር ወዳጅነታቸውን ካጠናከሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን በሩሲያ የሚያደርጉት  ጉብኝትም የዚሁ አንድ አካል እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡

ሁለቱ መሪዎች በሩሲያ ቭላዲቮስቶክ የፓስፊክ ወደብ ላይ የሚገናኙ ሲሆን በውይይታቸው በዋናነት ከአሜሪካ ጋር የገቡበት የኒዩክሌር መርሀ ግብር ቀዳሚ አጀንዳ እንደሚሆን ነው የተነገረው፡፡

ፒዮንግያንግ በምትገነባው የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ሩሲያ ድጋፍ ስታደርግ እና አሜሪካንም ስትቃረን መቆቷን ተከትሎ ሁለቱ መሪዎች በውይይታቸው የጋራ አቋም ሊይዙ ይችሉ ይሆናል እየተባለም ነው፡፡

ባሳለፍናቸው ጥቅት ወራት ውስጥ የኮሪያ ልሳነ ምድር ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራዋን ካቆመች እና የኒዩክሌር ጣቢያዎቿን ከዘጋች በኋላ የተረጋጋ ቢምስልም አሁንም ግን ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር መተማመን ላይ መድረስ አልቻለችም፡፡

ኪም ጆንግ ኡን ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ለሁተኛ ጊዜ በኒዩክሌር አቋሟ ዙሪያ ለውይይት ቢቀመጡም መፍትሄ የሚመጣ ስላልመሰላቸው አሁን የሩሲያን ድጋፍ አጥብቀው ይሻሉ፡፡

የአሜሪካ የኒዩክሌር መልዕክተኛ ባለፈው ሳምንት ወደ ሞስኮ በማቅናት ከሩሲያው አቻቸው ኢጎር ሞርግሎቭ  ጋር ያሏቸውን ክፍተቶች በማጥበብ አብረው ለመስራት ተስማምተው መሄዳቸው ምናልባትም የሰሜን ኮሪያን እቅድ እንዳያደናቅፍባት ግን ስጋት ሆኗል፡፡

(ምንጭ፡-  ሪውተርስ)