ኪም ጆንግ ኡን ወታደራዊ ኃይሉ የጦር ግንባሩን ዝግጅት እንዲያጠናክር ትዕዛዝ ሰጡ

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሀገሪቱ ወታደራዊ ኃይል የጦር ግንባሮች የውጊያ ዝግጅት እንዲያጠናክሩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን የሀገሪቱ ብሔራዊ ሚዲያ ዘግቧል።

አሜሪካ በበኩሏ ህገወጥ የድንጋይ ከሰል ከሰሜን ኮሪያ ወደ ሌላ ቦታ ስትወስድ የነበረችን መርከብ ማገቷን ገልጻለች።

የሀገሪቱ የፍትሕ ሚኒስቴር የፒዮንግያንግ ዕቃ ጫኝ መርከብ የታገተችው ዓለም አቀፍ ማዕቀብን ተላልፋ በመገኘቷ ነው ብሏል።

በሌላ በኩል ኪም የጦር ግንባሮች ሙሉ የተጠንቀቅ ዝግጅት እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውን ኬሲኤንኤ በዘገባው አትቷል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ኪም ጆንግ ኡን ለሁለተኛ ጊዜ ባደረጉት ውይይት በሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር መርሃ ግብርና በማዕቀቡ ዙሪያ ሳይስማሙ መቅረታቸው ይታወሳል።

የሁለቱ መሪዎችን ሳይግባቡ መለያየት ተከትሎ ዋሽንግተንና ፒዮንግያንግ ወደ ፍጥጫ ገብተዋል።

ሰሜን ኮሪያ በኪም  ምልከታ የተደረገበት ሚሳኤል የማስወንጨፍ ስራዋን በሳምንት ሁለት ጊዜ አካሂዳለች።

ኪም ባስተላለፉት መልዕክት በተለይ በምዕራብ ግንባር ያለው የሀገሪቱ ጦር ዝግጅቱን እንዲያጠናክር፣ የድንገተኛ የማጥቃት ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያደርግ አሳስበዋል።

መሪው የሰሜን ኮሪያ ሰላም፣ ደህንነትና ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው በሀገሪቱ ጠንካራ ወታደራዊ  ኃይል ደጀንነት ነው ብለዋል።

(ምንጭ፦ ሬውተርስ)