የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሩሃኒ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን ገለጹ

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሩሃኒ የአሁኑ ወቅት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረውን ውጥረት በውይይት ለመፍታት ጊዜው ምቹ አለመሆኑን ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡

በቅርቡ አሜሪካ የጦር መሳሪያ የጫኑ መርከቦችና ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ መላኳን ተከትሎ በሀገራቱ መካከል ውጥረት የነገሰ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም ሀገራቱ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ዝግጅቶችን ከማድረግ ባሻገር የጦፈ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትናንትናው ዕለት በትዊተር ገጻቸው እንዳስታወቁት፤ ኢራን ከአሜሪካ ጋር ጦርነት የምትገጥም ከሆነ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ጉዳይ ያበቃለታል ሲሉ ክፉኛ አስጠንቅቀዋል።

በአንፃሩ ኢራን በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት  ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማትፈልግና ገፍቶ የሚመጣ ከሆነ ግን የመመከት አቅም ያላት መሆኑን ገልፃለች።

ዋሽንግተን ባለፈው ሳምንት ነዳጅ በጫኑ የሳዑዲ መርከቦች እንዲሁም ከትናንት በስቲያ በኢራቅ ዋና ከተማ  ለተፈጸመው ሮኬት ጥቃት ኢራንን ትከሳለች።

ይህ ድርጊቷም  በቀጠናው በአሜሪካና አጋር ሀገራት ላይ የምታደርገውን ጥቃት አጠናክራ መቀጠሏን የሚሳይ መሆኑን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይናገራሉ።

የኢራን ፕሬዚዳንት ሀሰን ሩሃኒ ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ ደግሞ ኢራን በአሁኑ ወቅት ነገሮችን በውይይት ለመፍታት ፍላጎት የሌላት መሆኑን ተናግረዋል።

አለመግባባቶችን  በውይይትና በዲፕሎማሲያዊ መንግድ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ሩሃኒ፥ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ኢራን ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያሰችላት ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን ጠቁመዋል ።

ስለሆነም  ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በቀጠናው የተከሰተውን ችግር በውይይት ከመፍታት  ይልቅ እራስን መከላከል አማራጭ አድርጋ የምትጠቀም መሆኑን ነው ፕሬዚዳነቱ የገለጹት ።

ይህ የኢራን ውሳኔም  ሀገራቱ በአሁኑ ወቅት የገቡበትን ውዝግብ ይበልጥ እንዳያባብሰው ተሰግቷል ።

(ምንጭ፡-ሬውተርስ)