ሆንግ ኮንግን ከቻይና ጋር የሚያስተሳስረው ረቂቅ ህግ በገጠመው ተቃውሞ እንዲቆይ ተወሰነ

የሆንግ ኮንግን ግዛትን ከቻይና ጋር ያጋምዳታል የተባለለት ረቂቅ ህግ በገጠመው ታቃውሞ ሳቢያ ለጊዜው እንዲቆይ ተወሰነ፡፡

የቻይና ግዛት ተደርጋ የምትጠቀሰው፣ በንግድ ላይ በተመሰረተው ምጣኔ ሃብቷም በቁንጮነት የምትነሳው ሆንግ ኮንግ በአሁን ወቅት አሜሪካ፣ ሲንጋፖር እና ታላቋ ብሪታኒያን ጨምሮ ከ20 ሃገራት ጋር በሁለትዮሽ የሚያስተሳስራትን የbilateral extradition ስምምነቶች አሏት፡፡ ይሁንና በግዛቲቱ ገዢዎች አሁን ወጥቷል የተባለው የሁለትዮሽ ስምምነት ረቂቅ ህግ በዚህ ውስጥ ከማትካተተው ቻይና ጋር በሚስጥር የተቆራኘ ነው የሚል ስጋት አስነስቷል፡፡

በዚህ ረቂቅ መሰረት በምርጫ ምክር ቤት ይሁኝታ የተመረጡ፣ ተጠያቂነቱም ለቻይናም መንግስት የሆነው የግዛቷ ዋና አስተዳዳሪ በአስተዳደሩ ማንኛውንም አይነት ውሳኔ ለማስተላለፍ ስልጣኑ በእጃቸው ነው የሚል ሃሳብ ተካቶበታል፡፡

ሉግኮ የሚል ስያሜ የተሰጠው ባለ 70- አባላቱ የህግ አውጪ ምክር ቤት ስልጣኑ ከአስተዳደር ሃላፊው በታች ነው፡፡

ታዲያ ይህን ረቂቅ ህግ በመቃወም መዲናይቱን አጥለቅልቆ የነበረው የእሁዱ ሰልፍ እነዚህን ነጥቦች በሙሉ ያወግዛል፡፡

ሰልፉ ዛሬም ሲቀጥል በህግ አውጪው ቢሮ ፊት ለፊት ጥቁር ቲሸርትን በመልበስ የተደረገው ሰልፍ ምክር ቤቱ የከተማዋን ነዋሪ መብት ረግጧል የሚል ይዘትም አለው፡፡

ለጊዜው ይቆየን በተባለው በዚህ ረቂቅ ምክኒያት የተደረገውን ሰልፍ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስም በአየርም ጭምር በመጠቀም እየበተነ ነው፡፡ "ሆንግ ኮንግ ሆንግ ኮንግ!" የሚል ጩኸትም ከተማዋን እያናወጣት ይገኛል፡፡፡

በሆንግ ኮንግ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን እንሻለን የሚሉ ሰልፈኞቹ ላለፉት 5 ዓመታት ቻይና በከፊል ነጻዋ ግዛት በርካታ የሃይል እርምጃዎችን በመውሰድ በቁጥጥሯ ስር አስገብታናለች የሚልም ታክሎበታል፡፡

ማርክ የተባለው የ20 ዓመት ተማሪ ለአልጀዚራ እንደገለጠው የተቃውሞ ሰልፉን የተቀላቀለው ቻይናን ስለማያምን መሆኑን ያስረዳል፡፡

"የህግ የበላይነት በግዛቷ እንድሰፍን እንሻለን የሚለው ይህ ወጣት ቻይና በእጅ አዙር ነጻነታቸውን ልትነጥቃቸው እንደምትችልም በመስጋት ሃሳቡን ለአልጀዚራ አብራርቷል፡፡

የሆንግ ኮንግ ሰልፈኞቹ ከ2014ቱ ተቃውሞም በላይ ህዝቡ ለነጻነቱ ቆርጦ መነሳቱን እያስረዱ ናቸው፡፡

ባለ 70 መቀመጫው የ ሌግኮ አባላትንም ለቻይና የሚሟገቱ በሚል ነው የተቃውሞ ሰልፍ ተሳታፊዎቹ የሚገልጹት፡፤

በወንጀለኛ መቅጫነት የተቀመጡ የህግ ረቂቆች ተፈጥሮአዊ እና ሰብዓዊ መብቶችን የሚገፉ ናቸው በሚል ነው ለተቃውሞ የቀረቡት፡፡

በዛሬው ዕለት የህግ አውጪ ቢሮን በመክበብ ድምጽ እያሰሙ የሚገኙትን ተቃዋሚዎች ለመከላከል ከ5 ሺህ በላይ ፖሊሶች ታጥቀው መሰናዳታቸውን የአልጀዚራዋ ዘጋቢ ሳራ ክላርክ ከስፍራው ዘግባለች፡፡

ከስፍራው የምትዘግበው ጋዜጠኛ ክላርክ አሁን ነገሮች ሁሉ በግዛቷ ዋና አስተዳዳሪ ኬሪ ላም የውሳኔ ለውጥ አሊያም በተቃዋሚዎች የአላማ ጽናት ላይ ወድቋል ብላለች፡፡

የተለያዩ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም በረቂቅ ህጉ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ እየገለጹ ነው፡፤ ዋና አስተዳዳሪዋ ኬሪ ላም ግን በአቋማቸው ጸንተዋል፡፡

ምንም እንኳ ረቂቁን ለጊዜው ቢያቆዩትም ተግባራዊ ማድረግ የግድ እንደሚላቸውም አሁንም ይሟገታሉ፡፡

ሆንግ ኮንግ እስከ ፈረንጆቹ 1997 በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረች እና ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግን በቻይና ስር እየተዳደረች ያለች ከፊል ሉዓላዊት ግዛት ተደርጋ ትጠቀሳለች፡፡