እስራኤል በጎላን ኮረብታ የምትመሰርተውን አዲስ ከተማ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ስም ሰየመች

እስራኤል በጎላን ኮረብታ የምትመሰርተውን አዲስ ከተማ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስም ሰየመች።

እስራኤል በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ወቅት ከሶሪያ በማረከችው የጎላን ኮረብታ ውስጥ የምትመሰርተውን አዲስ ከተማ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስም ሰይማለች ።

የክብር ስያሜው የተሰጠውም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጎላን ኮረብታዎች የእስራኤል ግዛት አካል መሆናቸውን ዕውቅና በመስጠታቸው ነው ተብሏል።

በስያሜ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለእስራኤል ባላቸው አጋርነት እና ቁርጠኛ አቋም የክብር ስያሜ የተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ መሰረትም እስራኤል በዓረብ እስራኤል ጦርነት ወቅት ከሶሪያ በነጠቀችውን የጎናል ኮረብታ ውስጥ የሚመሰረተው አዲስ ከተማ ለፕሬዚዳንቱ ክብር ሲባል በስማቸው መሰየሙን አስታውቀዋል።

ስለሆነም የሚመሰረተው አዲስ ከተማ  ስያሜ “ትራምፕ ኮረብታ” ተብሎ የሚጠራ ይሆናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ።

ስያሜውን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ትራምፕ የእስራኤል ህዝብና መንግስት ለሰጣቸው ታላቅ ክብር በትዊተር ገፃቸው ምስጋና አቅርበዋል ።

ይሁን እንጂ እስራኤል ቦታውን በፕሬዚዳንት ትራምፕ ስም የሰየመችበት መንገድ ህጋዊ አሰራርን የተከተለ አለመሆኑ በዘገባው ተመላክቷል።

አዲስ የሚመሰረተው ከተማ ከሶሪያ ዋና ከተማ ደቡብ ምዕራብ እቅጣጫ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ስፋቱም በአጠቃላይ 1ሺህ ኪሎ ሜትር ቦታ ይሸፍናል።

እስራዔል የጎላን ኮረብታዎችን ከሶሪያ የወሰደችው በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የዓረብ-እስራዔል ጦርነት ወቅት መሆኑ ይታወሳል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።