የመንግስታቱ ድርጅት የጥላቻ ንግግርን ለመታገል የሚያስችል ቻርተር አረቀቀ

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጥላቻ ንግግር ላይ ጦርነት አውጀዋል፤ ለአባል አገራት እንደተናገሩት " እርስ በእርስ በመተያየት የተሻለ ማድረግ አለብን” ብለዋል፡፡

"የጥላቻ ንግግር ስር ሰዶ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን አሁን ትኩረት አግኝቷል" ያሉት ጉቴሬዝ የመንግስታቱ ድርጅት በጥላቻ ንግግር ላይ ስትራቴጂ እና እቅድ መጀመሩን ተናግረው "ትግላችንን አናቆምም" ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ስትራቴጂው እና የትግበራ ዕቅዱ አዲስ ቢሆንም መድልዎን በማስወገድ የሁሉንም ሰብአዊ መብት ለማክበር መሰረት ይሆናል ተብሏል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት ቻርተር የረቀቀው በአይሁዶች ላይ በተነሳ የጥላቻ ንግግር በሆሎኮስት የተደረገውን የዘር ጭፍጨፋ ተከትሎ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ይህ ድርጊት ከተፈጸመ 75 ዓመታት በኋላ፤ ጎቴሬዝ በኒው ዮርክ በሚገኘው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ተሰብስበው ለነበሩት ልዑካን እንደተናገሩት "ይህን ትምህርት ከረሳን አደጋ ላይ ነን" ብለዋል፡፡

የጥላቻ ንግግሮችና አፍራሽ አስተሳሰቦች በዲጂታል ቴክኖሎጂ በኩል በስፋት እየተሰራጩ መሆኑን የገለጹት ዋና ጸሓፊው አክራሪዎች ኦንላይን ተሰባስበው የአዳዲስ አክራሪዎች ምልመላን ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

የጥላቻ ንግግር የሰብአዊ መብት ጥሰት ከመፈጸምም በተጨማሪ የማህበራዊ ትስስርንና የጋራ እሴቶችን በመሸርሸር ለግጭት ይዳርጋል ብለዋል ዋና ጸሓፊው፡፡

የጥላቻ ንግግር በሩዋንዳ፣ በቦስኒያ፣ በካምቦዲያ በተፈጸው የዘር ጭፍጨፋ እና በቅርቡ በሲሪላንካ፣ በኒው ዚላንድ እና በአሜሪካ በአምልኮ ቦታዎች ላይ የተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ በጥላቻ ንግግር ምክንያት እንደሆነም ዋና ጸሓፊው መናገራቸውን ከዩ ኤን ኒውዝ ሴንተር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡