አሜሪካ በኦማን ባህረ ሰላጤ አካባቢ የነዳጅ ጫኝ ታንከሮች ላይ ለደረሰው ጥቃት ኢራን ሀላፊነቱን እንደምትወስድ ገለጸች

ኢራን በኦማን ባህረ ሰላጤ አካባቢ በሁለት የነዳጅ ጫኝ ታንከሮች ላይ ለደረሰው ጥቃት ሀላፊነቱን ትወስዳለች ሲሉ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴርን በጊዜአዊነት እየመሩ ያሉት ማርክ ኢስፐር ተናገሩ፡

ሚኒስትሩ ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል ሀገራት መከላከያ ሚኒስትሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው ይህን የተናገሩት፡፡

ኢራን ከሰሞኑ ሉዓላዊ ድንበሬን ተሻግሯል ያለችውን የአሜሪካ ሰው አልባ የቅኝት አውሮፕላን መታ መጣሏን ተከትሎ አሜሪካም ለጥቃቱ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅታ እንደነበርና ወደ ኋላ ላይ ግን ሀሳቧን እንደቀየረች ፕሬዝዳንት ትራምፕ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ምንም አይነት ጦርነት እንደማትፈልግ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ኢራን ወደ ጦርነት የምትገባ ከሆነ ሀገሪቷ ትጠፋለች ሲሉ መናገራቸውም የሚታወስ ነው፡፡

የዶናልድ ትራምፕን  አስተያየት ተከትሎ የኢራን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ አባስ ሞሳቪ ኢራን ከአሜሪካ ለሚሰነዘርባት ማንኛውንም አይነት ጥቃት ጠንካራ አጸፋዊ ምለሽ ትሰጣለች ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴርን በጊዜአዊነት እየመሩ ያሉት ማርክ ኢስፐር አሜሪካ ከኢራን ጋር በገባችበት እሰጣ እገባ ዙሪያ ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል ሀገራት መከላከያ ሚኒስትሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ዋሺንግተን በምንም አይነት ሁኔታ ከቴሄራን ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የኢራንን ማንኛውም አይነት ጸብ አጫሪ ተግባር እንደማይታገሱም  አስታውቀዋል፡፡

ኢራን በኦማን ባህረ ሰላጤ አካባቢ በሁለት የነዳጅ ጫኝ ታንከሮች ላይ ለደረሰው ጥቃት ሀላፊነቱን ትወስዳለች ሲሉ ሚኒስትሩ ከሰዋል፡፡

ነገር ግን ሁኔታው እንዲባባስ ሀገራቸው ፍላጎት እንደሌላት መግለጻቸውን በውይይቱ የተሳተፉ የጥምረቱ ዲፕሎማቶች ተናግረዋል፡፡

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ዋና ጸሀፊ ጀነራል ጀንስ ስቶልተንበርግ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሜሪካ ከኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ ላለመግባት ያላትን አቋም በግልጽ ያስቀመጠችበት መድረክ እንደነበር ጠቁመው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኢራን ጋር በግልጽ ለመነጋገርም ውሳኔዋን አሳውቃለች ብለዋል፡፡

የፈረንሳዩ መከላከያ ሚኒስትር ፍሎረንስ ፓርሊ አሜሪካ በኦማን ባህረሰላጤ ላይ በምታካሂደው ማንኛውም አይነት ወታደራዊ ተልዕኮ የኔቶ አባል ሀገራትን እንዳታሳትፍ ለአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ማሳሰቢያ አዘል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ዘገባው አመላክቷል፡፡

የቱርኩ መከላከያ ሚኒስትር በበኩላቸው ኢራን ላይ ማዕቀብ ከማስተላለፍ ይልቅ በቅርበት መነጋገር ዋነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሌሎች የኔቶ አባል ሀገራት መከላከያ ሚኒስሮችም ሁኔታው እንዳይባባስ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገልጸዋል ሲል ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡